ኤክቱስ ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም
በጌዴኦ ኮሬና እና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የአንዲዳ የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ኃላፊ በመጋቤ ምሥጢር ጥበቡ አናጋው የተዘጋጀው “ምሥጢራተ ማኅሌት ዘመላእክት (ቁጥር ሁለት)” የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በታላቅ ድምቀት ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።
የመጽሐፍ ምርቃቱ መርሃ ግብር ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና እና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መሪነት በጸሎተ ወንጌል ተከፍቶ የተጀመረ ሲሆን በመቀጠልም የዕለቱን ትምህርት መምህር መልአክ መሰለ በሰፊው አስተምረዋል። በተጨማሪም በመርሃ ግብሩ ላይ በዘማርያን ዝማሬ እንዲሁም በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቅኔ ቀርቧል።
በዚሁ የምርቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የሀገረ ስብከቱ የፕሮጀክት ማናጀር ቀሲስ ጤናው እንዳላማው ሰፊ የመጽሐፍ ዳሰሳ አቅርበዋል። ቀሲስ ጤናው በዳሰሳቸው ላይ እንደገለጹት ይህ መጽሐፍ በ፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያዊው ሊቅ በቅዱስ ያሬድ የተደረሱትንና በሰማያውያን መላእክት ሥርዓተ አምልኮ ላይ የተመሰረቱትን ረቂቅ ምሥጢራት፣ የዜማ ስልቶችንና የቅዱሳን መላእክትን የምሥጋና ምሥጢር ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጋር በማገናኘት በሰፊው የሚተነትን የምርምር ሥራ ነው።
አዘጋጁ መጋቤ ምሥጢር ጥበቡ አናጋው ለመጽሐፉ ዝግጅት ቅዱሳት መጻሕፍትን፣ አምስቱን የያሬዳዊ ዜማ መጻሕፍትን፣ የሊቃውንት የአንድምታ ትርጓሜዎችን እንዲሁም ጥንታውያን ድርሳናትንና ገድላትን በዋቢነት መጠቀማቸው የመጽሐፉን ምሁራዊና ሥርዓታዊ ጥንካሬ ከፍ እንዳደረገው በዳሰሳው ተብራርቷል። መጽሐፉ ለመደበኛው አንባቢያን አስቸጋሪ ሊሆኑ የሚችሉትን የግዕዝ ቃላትና የዜማ ምልክቶች ወደ አማርኛ በሚገባ በመተርጎም፣ ምስጢሩ በቀላልና ማራኪ ስልት እንዲቀመጥ ማድረጉም ተገልጧል።
በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ አባታዊ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን በእምነትና በዕውቀት ለማደግ ንባብ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ምዕመን አንባቢ መሆን እንዳለበት አሳስበው ሰፊ መልዕክት አስተላልፈዋል። የምርቃቱ ሥነ ሥርዓትም በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቋል።

