በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ብፁዕነታቸው በአንዲዳ የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ተገኝተው ከደቀ መዛሙርት ጋር ተወያዩ!

ኤክቱስ ግንቦት 20/2018 ዓ.ም

ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በአንዲዳ የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል። በጉብኝታቸውም ዘንድሮ ትምህርታቸውን አጠናቀው ለምረቃ የሚበቁ ደቀ መዛሙርትን በማግኘት አበረታች አባታዊ ምክርና መመሪያ ሰጥተዋል።

በዕለቱ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ብፁዕነታቸው ደቀ መዛሙርቱ በቆይታቸው ያገኟቸውን መልካም አጋጣሚዎችና ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች በጥቅሉ ያደመጡ ሲሆን፣ በቀጣይም በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት ለአገልግሎትና ለሕዝበ ክርስቲያኑ መልካም አርአያነት እንዲያውሉት አሳስበዋል። ደቀ መዛሙርቱም ለተደረገላቸው አባታዊ ማበረታቻ ምስጋናቸውን አቅርበው የተጣለባቸውን መንፈሳዊ ኃላፊነት በታማኝነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው ከውይይቱ በተጨማሪ በማኅበረ ቅዱሳን አማካኝነት እየተገነባ የሚገኘውን አዲሱን የአብነት ትምህርት ቤት ሕንጻ ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን የፕሮጀክቱን አጠቃላይ የሥራ ሂደትና ያለበትን ደረጃ ገምግመዋል። ከዚህም ጋር አብሮ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚከናወኑ lየዶሮ እርባታና የንብ ማነብ ፕሮጀክቶችን ተመልክተው አበረታችነታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ መርሃ ግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ መንፈሳዊ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ምሕረቱ እና የሀገረ ስብከቱ የፕሮጀክት ማናጀር ቀሲስ ጤናው እንዳላማው ተገኝተው ማብራሪያና አስፈላጊውን ማስተባበር አድርገዋል።

Scroll to Top