በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ብፁዕ አቡነ ገሪማ በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ!

ኤክቱስ ግንቦት 22/2018 ዓ.ም

ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት በደብሩ እየተከናወኑ ያሉ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል። ይህ ጉብኝት በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ አጥቢያዎችን የልማት እንቅስቃሴዎችን በቅርበት ለመከታተል ከሚደረጉ መደበኛ የሥራ ጉብኝቶች አንዱ አካል ነው።

በአጥቢያው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በሙሉ አስቀድሞ በተቀረጸው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሠረት እየተመሩ ያሉ ሲሆን በተለይም ብፁዕነታቸው ከዚህ በፊት “አንድም መሬት ጾም ማደር የለበትም” በሚል ያስተላለፉትን መመሪያ ተፈጻሚ ለማድረግ የተጀመሩ መሆናቸው ተገልጿል። ይህ መመሪያ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታዎችና ክፍት መሬቶች በተገቢው መንገድ በማልማት ተቋማዊ የገቢ አቅምን ለማሳደግ ታስቦ የወጣ መሆኑም ተመልክቷል።

በዚሁ መሠረት ብፁዕነታቸው በደብሩ ይዞታ ውስጥ የለሙትን እንደ ቡናና እንሰት ያሉ ቋሚ ተክሎችን ጨምሮ ሰላጣ፣ ባቄላ፣ በቆሎ፣ ቀይ ሥር፣ አደንጓሬ፣ ጥቅል ጎመን፣ ቆስጣ፣ ካሮትና ቃሪያ የመሳሰሉ የጊዜያዊ ሰብሎች ልማትንና የተደራጀውን የዶሮ እርባታ ሥራ ተዘዋውረው ጎበኝተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በደብሩ እየተከናወኑ ያሉ የውኃ ልማት ሥራዎችንና በሀገረ ስብከቱ አማካኝነት በቦታው ላይ እየተገነባ የሚገኘውን የመንበረ ጵጵስና ሕንጻ ግንባታ ሂደት ተመልክተዋል።

ብፁዕነታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ በተሠሩት በእነዚህ የልማት ሥራዎች መኩራታቸውን የገለጹ ሲሆን በደብሩ ለሚገኙ ለሥራው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን ለግሰዋል።

በጉብኝት መርሃ-ግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ፣ የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አካላት እና የልማት ኮሚቴ አባላት የተገኙ ሲሆን የሥራዎቹን ዝርዝር አፈጻጸምና የወደፊት ዕቅዶችን በተመለከተ ማብራሪያ አቅርበዋል።

ብፁዕነታቸው ከቀረበው ማብራሪያና ከጉብኝቱ በኋላ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረጉት ቆይታ የቤተ ክርስቲያኑን ተቋማዊ አቅም ይበልጥ ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መመሪያ ሰጥተዋል። በተለይም የወደፊቱን የቦታ አጠቃቀም ሥርዓት ለማስተካከልና የአገልግሎት ጥራትን ለመጠበቅ ይረዳ ዘንድ በደብሩ የመቃብር ቦታ አጠቃቀምን በተመለከተ ወደፊት ሊሠሩ ስለሚገቡ ሥራዎችና መዘርጋት ስላለበት የተደራጀ የአሠራር ሥርዓት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳና ጥራት እንዲጠናቀቁ የተጠናከረ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት አሳስበው በጸሎት ፈጽመዋል።

Scroll to Top