በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

<<ምልእዎንኬ ለእላ መሣብክት ማየ -ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው >>  ዮሐ 2:7

➠ በወርኃ ጥር ከሚከበሩ ዐበይት በዓላት መካከል ጥር 12 ቀን  የሚከበረው  የገሊላ ክፍል በሆነችው በቃና ሰርግ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገው ታላቅ ተአምር አንዱ ነው ።
<<ነገርን ከስሩ ውኃን ከጥሩ >> እንዲሉ  አበው ነገሩም እንዳህ ነበር  ። አካል ከህልውና ተገልጾለት  የሥላሴን አንድነት ሦስትነት በስፋትና በጥልቀት የተናገረው ነባቤ መለኮት በመባል የሚታወቀው  ባለ ራእዩ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ   <<በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ >>  በማለት ሙሉ ታሪኩን ይጽፋል  ።
➠ ይህም ሰርግ የተደረገው የካቲት 23 /30 ዓ ም ሲሆን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ( የጥምቀትን በዓል የውኃው  ወደ ጠጅነት መለወጥ በዓል ) ጋር እንዲከብር አባቶቻችን ስለ ወሰኑልን  የጥምቀት ማግስት ጥር 12  በቃና ዘገሊላ ኢየሱስ ክርስቶስ በእመቤታችን አማላጅነት ያደረገው ታላቅ ተአምር በደማቅ ሁኔታ ይከበራል  ። አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕዳ ደብዳቤያችንን ይደመስስልን  ዘንድ ( ቆላ 2:4) ጥር  11 ቀን ዕለተ እሑድ  በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ( ማቴ 3:17) ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ልጅነቱን አስመስክሮ ሳይውል ሳያድር ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ ( ማቴ 4:1) ። በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ በሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ የመጣውን ሰይጣን ድል ነስቶ የካቲት 20 ቀን በዕለተ ቀዳም ከገዳመ ቆሮንቶስ ወጥቶ ቅዳሜ ለእሑድ  ገሊላ ገብቶ አድሯል ።   የገሊላ ክፍል በሆነችው በቃና  የተደረገውም ሰርግ ጌታ ከገዳም ከወጣ በሦስተኛው ቀን ማለትም  ማክሰኞ   ነበር ።  የዚህ ሰርግ ባለቤት ዶኪማስ ሲሆን በሰርጉ ላይ ይታደሙ ዘንድ ከወንድ እስከ ሴት ከመምህር እስከ ደቀ መዝሙር ያልጠራው አካል ከቶ አልነበረም ።

➠ የሚደንቅ ሰርግ ! ታዋቂ ስዎች ከላይ  ምስኪኖች  ከታች ፤ መምህሩ ከቤት ውጥ ደቀ መዛሙርቱ ከቤት ውጭ ያልታደሙበት ፤ሁሉም አብረው ያከበሩት ሰርግ ነበር ። በአምላካችን የተባረከ ፣  እመቤታችንና ሐዋርያት የተገኙበት ሰርግ ! የሙሽራው የዶኪማስ ልብ እንዴ በደስታ ይመላ ይሆን  ? ትዳሩስ እንዴት ያምር  ? ምንኛ  መመረጥ ምንኛስ መታደል ነው ! 
የጋብቻን ቅዱስነትና ክቡርነት የተማርነውም በሰርግ ቤት ተገኝቶ   ሰርግን ከባረከው  የቤተ ክርስቲያን ሙሽራዋ ከሆነላት ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው ።
ብዙዎች  ግን ጋብቻን የሚረዱበትና የሚኖሩበት ሕይወት የተስተካከለ ባለመሆኑ መሰላቸትና መናቆር የበዛበት ይሆናል ። በየፍርድ ቤቱ ሳይቀር በስፋት ያለውም ጉዳይ የፍች ጉዳይ ነው ።
➠ ### ጋብቻ በባልና ሚስት ፈቃድ ብቻ የሚመሠረት አይደለም ፤ በእግዘብሔር ፈቃድ ጭምር እንጂ ።

ጋብቻ ስንፈልግ የምንገባበት ሳንፈልግ ደግሞ የምንወጣበትም አይደለሞ ፤ እስከ መጨረሻ የምንኖርበት እንጂ ።

ጋብቻ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸም ፣ ሁለቱም አካላት አንድ የሚሆኑበት ምሥጢርም ነው  ( ሜቴ  19:6) ።

  ጋብቻ የተበረከ ስለሆነ  የተበረኩ ልጆችም የሚገኙበት ነው (ዕብ 13:4)  ።

የሚገርመው  ሰዎች ራሳቸው ያልፈለጉትን ግን በልጆቻቸው እንዲፈጸሙ የሚፈልጓቸው ሁለት ነገሮች አሉ ።
1, የሰርጋቸው ቀን ከቤተ ክርስቲያን ጋር ሳይተዋወቁ የክርስትና  ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ ሰዎች ሲሆኑ
2, ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በሆነ ጋብቻ የተጋቡ ሰዎች ልጆቻቸው ሥርዓት ባለመያዛቸው የሚያዝኑ ሰዎች ናቸው ።
  ### ልጆች ሥርዓትን ከማን  ይማሩ  ? ማንንስ ይከተሉ ? ተጠያቂውስ ማን ነው ?
አሁን በአለንበት ዘመን  በዓለም ላይ ሥርዓት አልባነት ከተስፋፋባቸው መንገዶች መካከል የጋብቻ ሥርዓት መረሳቱና ክቡር በሆነው ጋብቻ የሚወለዱ ልጆች አለመኖራቸው አንዱ ይመስለኛል ።

➠ የእመቤታችን አማለጅነት

የሰርጉም ታዳሚዎች ወደ መጡበት ሳይመለሱ ለሰርጉ ይበቃል ተብሎ የታሰበው የወይን ጠጅ ድንገት አለቀ፣ አገልጋዮች የሚያደርጉት አጥተው በጭንቀት ተውጠው ሰማይ ምድሩን ማየት ጀመሩ ፣የአገልጋዮች ፊት ጠቆረ ፣ አንገታቸውንም ደፉ ፤  ማጣት  ክፉ ነውና ያውም በሰርግ ቀን ሰው በተሰበሰበበት  !
ነገር ግን ይህን ጭንቀታቸውን ያየችው እመቤታችን ማንም ሳይነግራት  << የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም >>  ስትል ነበር  ወደ ልጇ  የማማለድ ስራዋን ያቀረበችው ።  አምላካችንም የእመቤታችንን ምልጃ ከሰማ በኋላ << አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም >>  አላት ፤ ማለትም አንቺ ያልሽኝን ላለማድረግ ምን ጠብ  አለኝ አደርግልሻለሁ ማለት ነው ። ይህም ሊታወቅ << የሚላችሁን አድርጉ >> ነበር ያለችው ፤ ምልጃዋን እንደ ተቀበላት ታውቅ ነበርና ። የእናት ልመና ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስ ነውና ነገሩ ።
➠  ስለ ምልጃዋ ስለ ርኅራኄዋ  <<ፈጣን ደመና >>  ( ኢሳ 19:1) ብሎ ነቢዩ ኢሳይያስ የገለጣት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዛሬም  ቢሆን በአማላጅነቷ  ትረዳናለች ታግዘናለች ። እኛም  << ወበእንተዝ ንስአል ኀቤሃ  ኵሎ ጊዜ ከመ ታስተሥሪ በእንቲኣነ ኀበ ፍቁር ወለዳ ሔርት ይእቲ በኀበ ኵሎሙ ቅዱሳን – ስለዚህ ሁልጊዜ ወደ እርሷ እንለምን ከተወደደ ልጇ ዘንድ ስለእኛ ይቅር ታስብለን  (ታማልደን) ዘንድ በቅዱሳን ዘንድ ቸር ናት >> እያልን እንደ ቅዱስ ኤፍሬም እንማጸናታለን ።
➠ ሌላው አሳብ << ጊዜዬ ገና ነው >> የሚለው ነው ።  ይህም ማለት ብዙ ትርጓሜ ቢኖረውም ዋናው አሳብ ግን ምሳሌው  ወይን የሆነለት ክቡር ደሙን  የዓለምን ኃጢአት ለማስተስረይ በመስቀል የሚያፈስበት ጊዜው  ዕለተ ዐርብ ገና ነው ማለቱ ነበር ። ይህውም አልቀረ ጊዜው ዕለተ ዐርብ ሲደር የዓለም ኃጢአት የሚሰረይበትን ክቡር ደሙን እንኩ ጠጡ ብሎ ሰጠን (ማቴ 26:28) ። በዚህ ክቡር ደም የዓለም ኃጢአት ተወገደ (ዮሐ 1:29) ፣ አነጻን ቀደሰን  << በውኂዘ ደሙ ቅዱስ አንጽሖሙ ለመሀይምናን ወለሕዝብ ንጹሓን >> እንዳለ  ቅዱስ ኤፍሬም  የዶኪማስን ሰርግ የፋሲካ ፤ የወይን ጠጁንም የክቡር ደሙ ምሳሌ አደረገው ።
ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ብሉ ጠጡ የሚል ለጋስ ያለ እርሱ ማን አለ ?
➠ ይህን ድንቅና ረቂቅ የሆነ ቃል በመናገር ዕለተ ሞቱን ከአስተማረ በኋላ የአገልጋዮቹን ጉድለት ይመላ ዘንድ በሰርግ ቤት የተገኘው አምላካችን  << ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው>> ብሎ አዘዘ ። የእመቤታችንን ምልጃ መቀበሉን የምንረዳውም ጋኖች በውኃ እንዲመሉ በማዘዙና ውኃውን ወደ ጠጅነት  በመለወጡ ነው፤ እመቤታችንም  የሚላችሁን አድርጉ ነበርና ያለችው ።
ባዶ የነበሩት  ስድስቱም የድንጋይ ጋኖች በውኃ ከተሞሉ በኋላ በአምላካዊ ሥራው በእመቤታችን አማላጅነት ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት ለወጠው ፤ እግዚአብሔር ሲል ሁሉ ይለወጣልና ።

➠ የሰው ልጅ ጉድለት የሚሞላው በምን  ይሆን  ?
የእኛስ ሕይወት የሚለወጠው መቼ ነው ?

ከላይ ነጭ ነጠላ ለብሰን እንመላለሳለን ውስጣችን ግን በብዙ ነገሮች ጠቁሯል ፣ ሰብከን ስንጨርስ ቃለ ሕይወት ያሰማልን እንባላለን ሕይወት ግን ከሁላችንም ጠፍቷል ፣ ዘምረን ስንጨርስ ከጣዕሙ ብዛት የተነሣ አጥንትን የሚያለመልም የመላእክትን ዝማሬ ያሰማልን እንላለን  ነገር ግን የለመለመና ጣዕም ያለው ሕይወት የለንም ።

➠ በአምላካዊ ትእዛዝ የተለወጠው የወይን ጠጅ ቀድሞ ከነበረው  እጅጉን ጣፈጭ  መሆኑን የቀመሰው አሳዳሪውም   ሙሽራውን  ጠርቶ   << ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል >> በማለት በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ የተለወጠውን ወይን  ማድነቅ ጀመረ  ። በእርግጥ እግዚአብሔር ያደረገው ነገር በሙሉ ከሁሉ በላይ ነውና   መርምረንና ተናግረን ስለማንጨርሰው  << ናርምም እስመ ኢንክል ፈጽሞ ጥንቁቀ ነጊረ በእንተ ዕበዩ  >>   እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም ሁሉን ቻይ መሆኑን  አድንቀን ዝም እንላለን ።

➠ ይህም ሰርግ የሰርግ ሥርዓት ብቻ የተፈጸመበት አልነበረም ውኃውን ከውኃነት ወደ ወይን ጠጅነት በመለወጡ ምሥጢረ ሥጋዌን በሥራ ገልጦ ያሳየበት ዕለትም ጭምር  እንጂ ፤ በኋላም በኬልቄዶን ጉባኤ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ  የልዮናውያንን አስተምህሮ ማለትም ሁለት ባሕርይ የሚለውን ትምህርት ሲቃወም መልስ የሰጠበት ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነበር ።
<< ወደ ሰርግ ቤት የተጠራ  ውኃውን ጠጅ ያደረገ  ማን ነው  ?>>  ብሎ ጠየቀ ። ሥጋ ካላችሁ የሥጋ ወደ ሠርግ ቤት መጠራት አያስደንቅም ፤ ብቻውንም ሥጋ ውኃውን ጠጅ ማድረግ አይችልም ፣ መለኮት ካላችሁ ውኃውን ጠጅ መድረግ ቢችልም ወደ ሰርግ ቤት መጠራት ግን አይችልም ብሎ እረቶበታል ። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም  አምላክ ፍጹም ሰው ነው ። አምላክ  ፍጹም ሰው እንደ መሆኑ ወደ ሰርግ ቤት ተጠርቷል ፤ ሰውም ፍጹም እምላክ እንደ መሆኑ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ቀይሮታል ።  ከተዋሕዶ በኋላ ይህ የሥጋ ፣ ይህ የመለኮት የምንለው ሥራ የለም ። በፍጹም ተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ስለሆነ ሥራውን  ሠራ ይባላል እንጂ ።
ይህም ተአምር በገዳመ ቆሮንቶስ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲራብ አይቶ ሰይጣን ርሑቅ ብእሲ መስሎት ነበርና የባሕርይ አምላክ መሆኑን ያሳየበት የመጀመሪያውና ታላቁ  ተአምር ነው ።

   ወስብሐት ለእግዚአብሔር  !!!

Scroll to Top