በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

‎ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለ2018 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ!

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር ለሚገኙ፣ የሀገሪቱን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ ለቆሙ፤ በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ለሚገኙ ብሎም የሕግ ታራሚዎች ሆነው በየማረሚያ ቤቱ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት፤ “እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ስምንት ዓመተ ምህረት የርእሰ ዐውደ ዓመት በዓል አደረሳችሁ!” ሲሉ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

‎ቅዱስነታቸው በአባታዊ መክልዕታቸው፤ “የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ የተለየ ክብርና ደረጃ እንዳለው በቅዱስ መጽሐፍ በተደጋጋሚ ተገልጾአል፣ ልዩ የሚያደርገውም ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ነው፣ ሰው ልዩ ፍጡር መሆኑን ከሚገለጽባቸው መካከል እግዚአብሔር በሦስትነቱ “ሰውን በአርአያችንና በአምሳላችን እንፍጠር በሚል ልዩ አገላለጽ መፈጠሩ፣ አፈጣጠሩም በእግዚአሔር መልክና አምሳል መሆኑ፣ በእግዚአብሔር እፍታ ሕያው ነፍስ እንዲኖረው መደረጉ፤ በሥልጣንም የፍጥረታት ሁሉ የበላይ ሆኖ መሾሙ ከሌሎች ፍጥረታት ልዩ ያደርገዋል” ብለዋል፡፡

‎”እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ሆነን እንድንኖር በእግዚአብሔር ስንፈጠር በሕይወት እንድንኖር ነው፣ እግዚአብሔር በምድር ላይ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሰውን ከአንድ ፈጠረ የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮም ይህንን ያመለክታል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አክለውም “ሰዎች በምድር ላይ በሕይወት እንዲኖሩ የተፈጠሩ ሆነው እያለ በሕይወት እንዳይኖሩ ማድረግ ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር መጋጨትን ያስከትላል በዘመናችን ዓለማችንን እየፈተነ ያለው ተቀዳሚ ፈተና ሰዎች በሕይወት እንዳይኖሩ የማድረግ ዝንባሌ ነው” ብለዋል።

‎”እንደዚህ ዓይነቱ ዝንባሌ በዓለም ባይኖር ኖሮ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድሆች ባሉበት ዓለም ለሰው ልጅ ሕይወት ማጥፊያ የሚሆን መሳሪያ ለማምረት ቁጥር ስፍር የሌለው ገንዘብ አይወጣም ነበር” በማለትም ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

‎ስለሆነም በሕይወት እንዲኖር የተፈጠረውን ሰው በሕይወት የመኖር መብቱን ከመንፈግ መቆጠብ የአዲሱ ዓመት ትልቁ አጀንዳ አድርገን ብንወስድ ለሁላችንም ይበጀናል በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

‎ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አክለውም፤ “ለኑሯአችን የሚያስፈልገንን ፍጆታ በበቂ ሁኔታ እንድናገኝ ላባችንን አንጠፍጥፈን መስራት ይገባናል፣ ይህም ከሠራን ያለጥርጥር የምናገኘው ነው፤ ሁለቱም የጎደሉብን በኛ አስተሳሰብ፣ አሠራርና አጠቃቀም እንጂ እግዚአብሔር ሳይፈቅድልን ቀርቶ ወይም ነፍጎን አይደለም”ብለዋል።

‎ነገር ግን እኛ በምንራመድበት በእግራችን ሥር ያለውን ሀብት ትተን በሩቅ ያለውን ስንመለከት ሁሉን ያጣን ሆነን በችግር ወድቀን እንገኛለን፤ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ እየተፈታተነን ያለው ይኸው የተሳሳተ እሳቤ ነው ብለዋል።

‎”ኢትዮጵያ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን አድርገን በማመን በእኩልነት፣ በአንድነትና በስምምነት ከመጠቀም ይልቅ ያ የኔ ነው ያም የኔ ነው በሚል አባባል ምን ያህል ዋጋ እየተከፈለ እንደሆነ እያየን ነው፣ ይህ ግለኝነት ያየለበት አስተሳሰብ ገታ አድርገን በእኩልነትና በአብሮነት የሚያሳድገንን አስተሳሰብ የተሻለ መግባቢያ ሊሆን ይችላል፣ አዲሱ ዓመት በአዲስ እሳቤ ካላጀብነው አዲስ ሊሆን አይችልም” በማለት ገልጸዋል።

‎ስለሆነም “አዲሱን ዓመት መልካም በሆነ አዲስ ሀሳብ ፣እግዚአብሔርንና ሰውን በሚያገናኝ ቅዱስ ተግባር፣ በልማት፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በዕርቅና በስምምነት እንድንቀበለው” ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፏል።

‎አዲሱ ዓመት ለሀገር ሰላምና ልማት፤ ለሕዝቦች አንድነትና ስምምነት እንደዚሁም አለመግባባትን በፍትሕና በዕርቅ ለመፍታት ከልብ የምንተጋበት መልካም የስኬት ዘመን እንዲሆንልን እንጸልይ በማለት ለመላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

©መረጃው የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል ነው

የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮቻችንን ይወዳጁ!

Facebook

https://www.facebook.com/Ge7de12o

Telegram

https://t.me/Gedeokoreburji

Tiktok

Tiktok.com/@gedeokoreburji

Instagram

https://www.instagram.com/gedeokoreburji?igsh=azJrOGdpbDN4cG4=

Youtube

Website – Eotc-gkb.org

Scroll to Top