በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ሐምሌ ሃያ ሁለት ቀን የሚከበረው የመልአኩ የቅዱስ ዑራኤል በዓለ ንግሥ በዲላ ዋለሜ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
መርሃግብሩ በሀገረ ስብከቱ ትምህርት እና ካህናት አገልግሎት ክፍል ኃላፊ በመልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ምሕረቱ የተመራ ሲሆን በደብሩ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘምርያን ያሬዳዊ ዝማሬ ከቀረበ በኋላ ለዕለቱ የሚስማማ ትምህርት በደብሩ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ማእምራን መምህር ሰሎሞን ፈጠነ ተሰጥቷል።
የደብሩ የግብርና የልማት ሥራ እንዲጠናከር ትልቅ ሥራ ላደረጉ ለአባ ገብረ አረጋዊ ረታ እና ለዲያቆን አምራች ገብረ ሥላሴ የምስጋና ስጦታ እና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የደብሩ የልማት ሥራ እንዲፋጠን የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ላደረጉ ሰዎች ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ሁሉም አድባራት የተለያዩ የግብርና ሥራዎችን በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይ አብያተ ክርስቲያናቱ ወደ አምራችነት ለማሳደግ እየተሰራ ያለውን ሥራ ገልጸው እንዲሁም በዓለ ንግሡን በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በመስጠት መርሃግብሩን በጸሎት ፈጽመዋል።




