በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከሚገኙ ስድስቱ ወረዳ ቤተክህነት ለተውጣጡ የቋንቋ ሰባኪያነ ወንጌል ወደ ስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከመግባታቸው በፊት ለሁለት ቀን የሚቆይ ሥልጠና ለመስጠት ከማህበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ጋር በመተባበር በተዘጋጀው መድረክ ላይ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተገኝተው አባታዊ መልዕክት እና ለአገልግሎት ዝግጁ በመሆን በቀጣይ ስለሚያከናውኑት አገልግሎት ትምህርት ሰጥተዋል።
በመልዕክታቸው በቀጣይ ወደ መጡት አካባቢ ሲሰማሩ ፈተናዎችን አልፈው በማገልገል አዲስ የሚጠመቁ አማኒያን አስተምሮ በማምጣት ፣ክርስቲያኖች በእምነታቸው እንዲጸኑ በማድረግ ንሰሐ የሚገቡ ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበሉ ቤተክርስቲያን ባለችበት ሆነ በተገኘው ቦታ ሁሉ በመዘዋወር ወንጌልን ማስተማርና ለሰማያዊ ፀጋ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል ።
በቀጣይም አዳዲስ የስብከት ኬላዎችን በማቋቋም በነባሮዎቹ በማስተማር በሚታይና በሚመዘን አገልግሎት ጊዜአቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበው የሁለት ቀን የሥልጠና ቋይታ መልካም እንዲሆን በመመኘት ማህበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል የሥልጠና ሙሉ ወጪውን በመሸፈን መምህራንን በመመደብ ለሥልጠናው ስኬት ላበረከቱት ምስጋና አቅርበዋል ።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች የማህበረ ቅዱሳን ዲላ ማዕከል አመራሮችና የሥልጠናው አስተባባሪዎች አሰልጣኝ መምህራን ተገኝተዋል።



ኤክቱስ ሰኔ 27/2017 ዓ.ም