በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

የአብነት ትምህርት ቤት ለመሥራት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ!!

ኤክቱስ ኅዳር 13/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በአንዲዳ መድኃኔዓለም ለሚያስገነባው የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጸሎትና ቡራኬ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

ዝማሬ፣ ትምህርተ ወንጌልና በደቀመዛሙርት ቅኔ ቀርቧል።

የአንዲዳ መድኃኔዓለም የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ሁለት የመጻሕፍት ደቀ መዛሙርት ቅኔ ቀርቧል።

መምህር ዋስይሁን በላይ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አስፈጻሚ ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ኃላፊነት መሠረት የማኅበሩን አባላትና መላው ምዕመናንን በማስተባበር ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች በሁለንተናዊ አገልግሎት ራሳቸውን እንዲችሉና ተተኪ ሊቃውንትን እንዲያፈሩ 1991 ዓ.ም ጀምሮ ከአንድ መቶ ሰባ በላይ የገቢ ማስገኛና የአገልግሎት መስጫ ፕሮጀክቶችን ሠርቶ ማስረከቡን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ማኅበሩ በ2018 ዓ.ም ለመተግበር ከያዘው ዕቅድ መካከል በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን በማስተባበር በአንዲዳ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት ለመገንባት መዘጋጀቱንና ግንባታውም 14 ወራትን እንደሚቆይ ገልጸዋል። በተጨማሪም ማኅበሩ ከሀገረ ስብከቱ ጋር በጋራ መሥራት የሚስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ ጋባዥነት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን እጅግ በጣም ብዙ ገዳማትን ከመበተን ከማዳኑ በተጨማሪ በርካታ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር ቀዳሚ ተግባሩ መሆኑን ከመግለጻቸው በተጨማሪም ከማኅበሩ ጋር በርካታ ሥራዎችን በጋራ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

በመጨረሻም ግንባታ ለመጀመር የታሰበበት ቦታ እንዲሁም ላለፈው አንድ ዓመት የአብነት ትምህርት ቤቱ መንፈሳዊ ትምህርት ሲሰጥበት የነበረው የተማሪዎች ማደርያ፣ ጽሕፈት ቤት፣ የመማርያና የመመገቢያ ክፍሎች በተጨማሪም ወደፊት የተለያዩ ልማቶችን ለመሥራት የታሰበበት ቦታ ጉብኝት ተደርጎ የመርሃግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።

Scroll to Top