ኅዳር ፲፪ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት በሙሴ መሪነት እግዚአብሔር እስራኤልን ከግበፅ ባርነት ነጻ ማውጣቱን የምናከብርበት በዓል ነው ። ይኸውም ወጡ ለማለት ወረዱ ማለት ይቅድማልና በምን ምክንያት እንደወረዱ እንመልከት።እስራኤል ማለት ሕዝበ እግዚአብሔር ማለት ሲሆን ሥርዎ ሃይማኖት በመባል የሚታወቀው የአብርሃም የልጅ ልጅ ለያዕቆብ የተሰጠ ስም ነው ። ይህ ሕዝብ በታላቁ በአባቱ በአብርሃም በኩል ዘርህን እንደ ሰማይ ኮከብ አበዛዋለሁ የተስፋይቱንም ምድር አወርሰዋለሁ ተብሎ የተነገረለት እግዚአብሔርም የማዳን ሥራውን ለመስራት ያቀደበት ቢሆንም ቅሉ ዘፍ ፲፭ ፥፭-፲፪ በተቃራኒው ደግሞ ከዚሁ ምዕራፍ ሳንወጣ ዘፍ ፲፭ ፥፲፫ ላይ ስንመለከት
“ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ፤ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል።ተብሎ ትዕቢት ተነግሮበት የነበረ ሕዝብ ነው። በጣም የሚገርመው ይህ ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆን የተስፋይቱን ምድር (ከነዓንን) እንደሚወርስ እግዚአብሔር ወልድም ከእርሱ ተወልዶ እንደሚያድነው ተስፋ ቢኖረውም በሌላ በኩል ደግሞ ለ፬፻ ዓመት በስደት ፣በባርነት ፣ በሰቆቃና በኀዘን እንደሚኖር ተነግሮበት ነበር።
የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ግድ ነውና ይህ ትንቢት በተነገረ በ፪፻ ወ ፲፭ ዓመት እስራኤል የተባለው ያዕቆብ እርሱና ቤተሰቦቹ ፸ ሆነው ወደግብፅ መሰደዳቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ለጊዜው በሀገራቸው የተከሰተውን የረሀብ ዘመን በወንድማቸው በዮሴፍ አማካኝነት በጥጋብ ቢያልፉትም በኋላ ግን በተለይም የወንድማቸው የዮሴፍን ሞት ተከትሎ የመጣባቸው መከራ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አልነበረም። (በዘጸ ፩፥፰ በግብፅም ዮሴፍን ያላወቀ አዲስ ንጉሥ ተነሣ )ተበሎ እንደተጻፈው ይህ ንጉሥ የዮሴፍን ደግነት ፣ ጥበብ ፣ ክብር እና መጋቢነት ያላወቀ፣ ልቡ በክፋት የጸና፣ አንደበቱ በበቀል የተመላ፣ የሰይጣን ግብር አስፈጻሚ ነበር ማለት ብቻ ሳይሆን እርሱም ሥጋ የለበሰ ሰይጣን ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም ።
ከዚህ ሰው ንግሥና በኋላ በእስራኤል ላይ ፅኑዕ የሆነ መከራ መጣባቸው ። በደስታቸው ላይ ኀዘን፣ በእረፍታቸው ላይ ስቃይ፣ በልተው በማደራቸው ፋንታ ረሀብ፣በክብራቸው ፋንታ ውርደት መጣባቸው በእስራኤላውያን መብዛት እረፍት ያጣው ፈርዖን ዘጸ፩፥፲ ስንመለከት (እንዳይበዙ፥ ሰልፍም በተነሳብን ጊዜ ጠላቶቻችንን አግዘው እንዳይወጉን ከምድሪቱም እንዳይወጡ፥ ኑ እንጠበብባቸው፡” አለ) ይለናል። ፈርዖን እስራኤላውያንን ለማጥፋት ጥበብን ይሻ ነበር እግዚአብሔር ያበዛውን ማጥፍት ባይቻልም ፈርዖን ግን ፍላጎቱን ለማሟላት የጥፋት ጥበብን ፈለገ። ሰው ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሲወጣ ሀሳቡ የጥፋት፣ ጥበቡ የጥፋት፣ ግብሩ የጥፋት አመለካከቱ ሁሉ የጥፋት ይሆንበታል ። ፈርዖን ሀሳቡን እውን ለማደረግ በእስራኤላውያን ላይ በዙ ግፍ የፈጸመ ሲሆን የተወሰኑት፦
ጡብ ማስጣል
ኖራ ማስወቀጥ
ጭቃ ማስረገጥ
ፈርዖን እስራኤላውያንን በእነዚህና በመሳሰሉት ስራዎች እያሰቃየ ፌቶም ፣ ራምሴና ዖን የሚባሉ ሦስት ከተሞችን በእነሱ ላብ ፣ ጉልበትና ደም አስገንብቷል ።ፈርዖን ከዕብራውያን ስዎች አንድም ሰው ለቅጽበት ስንኳ እረፍት ማግኘት እንደሌለበት ትእዛዝ ሰጥቷል ።ይህንም ያደረገው በሁለት ምክንያት ነው ፦
፩ኛ በስራ ተጠምደው ከዋሉ የጦር ልምድ አይኖራቸውም ከጠላቶቻችንም ጋር ተባብረው አያጠፋንም ብሎ ነው ። ፪ኛ ወንዶች ጭቃ ሲረግጡ ሴቶችም ኖራ ሲወቅጡ ከዋሉ ወንዶችም ወደ ሴቶች ፣ ሴቶችም ወደ ወንዶች አይደርሱም በዚህ ምክንያት ዕብራውያን እንዳይወልዱና እንዳይበዙ ለማድረግ ነበር። እውነት ለመናገር በዕብራውያን ላይ የደረሰው ግፍ መጠን የሌለው ነው ፣ ምጥ የተያዘች እናት ስንኳ ያለእረፍት እያማጠች ጭቃ የረገጠችበት ዘመን ነው ።
በዚያ ዘመን አንዲት ራሔል የምትባል ፣ውድ ባለቤቷ ሮቤልን በሞት ያጣችና መንታ የጸነሰች እናት ነበረች። በባለቤቷ ፋንታ ጭቃ እንደትረግጥ ተገደደች፣ በዚያን ሰዓት ምጥ መጣ ፣አምጣ ለመውለድ እኳን ፈቃድ ብትጠይቅ አልተፈቀደላትም ።እያማጠችም ጭቃ እየረገጠችም በነበረችበት ሰዓት ወለደች። ሆኖም ራሔል የነበረችው አልጋላይ ሳይሆን ጭቃ ላይ ስለሆነ መንተኞች ልጆቿ ከወደ ጭቃው ተቀላቀሉ ።የልጅ ፍቅር ያንገበገባት ራሔል ምጧን ረስታ ልጆቿን ለማንሳት ብትሞክሮም ከጭቃው ጋር አብራ እንድትረግጣቸው ተገደደች።የሰው ደም ግንብ ያጸናል ተብሎ ተነገረ ።ዛሬም በሀገራችን የሰው ደም ግንብ ያጸናል የተባለው የግብፅ አዋጅ የታወጀ ይመስላል ምን አልባት ፈርዖን ወደኢትዮጵያ መጥቶ ይሆን? እናም ራሔል እንባዋን ወደ ሰማይ ረጨች የራሔል እንባ የዕብራውያንን እንባ ቅድመ እግዚአብሔር አደረሰች እግዚአብሔርም ሰማቸው። ሙሴንም ከግብፅ እንዲያወጣቸው ላከላቸው ።
ዕብራውያንን ነፃ ለማውጣት እግዚአብሔር ሙሴን አስነሳ።ከሚቀበሉት መከራ አንዱ የእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች መገደል ነበር።በዘጸ ፩፣፲፮ እንደምናነበው ፎሀ እና ሲፓራ የተባሉ የግብፃውያን ሴቶች የዕብራውያንን ሴቶች አንዲያዋልዱ እና ወንድ ከተወለደ ደግሞ እንዲገድሉ ከፈርዖን ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነብር።በዚህ መሠረት ከእስራኤል ወንድ ልጅ ሲወለድ ይሞት ነበር ከዚህ የተረፈውም በባሕር ይጣል ነባር ። ሙሴን ግን እግዚአብሔር ጠበቀው።በንጉሡም ቤት ለ፵ ዓመት አኖረው ።እስራኤልን ይታደግ ዘንድ እግዚአብሔር መርጦታልና።በኋላም ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር ሙሴን በ፹ ዓመቱ ወደግብፅ ላከው ።ሙሴ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ተአምር ለፈርዖን ካሳየ በኋል ሕዝቤን ልቀቅ ይልሀል እግዚአብሔር አለው ።ፈርዖንም እግዚአብሔርን አላውቅም ሕዝቤንም አለቅም በማለት ልቡን በክፋት አጸናው።በፈርዖን የልቡና ክፋት ምክንያት እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ዘጠኝ መቅሰፍት አስረኛ ሞተ በኩርን አመጣባቸው።በተቃራኒው ዕብራውያንን ግን ከዚህ ሁሉ መቅሰፍት እየጠበቀ ያበዛቸው ነበር።የፈርዖን አመጽ ካመጣው መቅስፍት አንዱ የግብፅ ውሃዎች በሙሉ ደም መሆን ነበረ የግብፅ ሰዎችም ለሰባት ቀን የሚጠጡት ውሃ በማጣት አልቀዋል። በመጨረሻም ሞተ በኩር መጣ የግብፅ ምድርም ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ የበኩር የሆነውን (መጀመርያ የተወለደውን)በሞት አጣች ።ዘጸ ፲፪፣፲፪
ዕብራውያንን ግን ይህ ሁሉ እንዳያገኛቸው የአማናዊው በግ የክርስቶስ አምሳል የሆነውን የፋሲካውን በግ አርደው ስጋውን እንዲበሉ ደሙንም የቤታቸውን በር እንዲረጩት እግዚአብሔር ለሙሴ አዝዞት ስለነበር ሞተ በኩር ከበራቸው እደረሰ ተመልሷል።ከዚህ በኋላ የሚመራውን ሕዝብ በሞት ያጣ ፈርዖን ዕብራውያን የሶስት ቀን መንገድ ሄደው መስዋዕት ሰውተው እንዲመለሱ ፈቀደላቸው ።እስራኤላውያን ግን ለብዙ ዘመን የተገዙበትን ወርቅና ብር በተውሶ ምክንያት ይዘው ወጥተዋል ። ውስጡ ግን ጥበበ እግዚአብሔር ነበር ።ፈርዖን ከመከራው ጽናት የተነሳ በፈቃዱ ቢለቃቸውም ተከትሎ ማሳደዱን ግን አልተወም ነበር።
እግዚአብሔርም ዕብራውያንን በሰባት ደመና እየመራ ጠበቃቸው
፩ኛው ከላይ የፀሐይን ሙቀት ይከላከላል
፪ኛው ከስር እንቅፋት እንዳያገኛቸው
፫ኛው በቀኝ ጠላት እንዳይጎዳቸው
፬ኛው በግራ ከሚመጣ ጠላት ይጠብቃል
፭ኛው በኋላ ከሚመጣ
፮ኛው በፊት ከሚመጣ
፯ኛው የሶስት የአራት ቀን መንገድ ሲጠርግላቸው ውሎ ማታ ያበራላቸው ነበር። ፈርዖንም ተከትሏቸው ባሕረ ኤርትራ ሲደርሱ ድምጻቸውን እየሰማ ሳያገኛቸው የቀረው በደመና ስለተከበቡ ነው ።እስራኤልን በፊታቸው የኤርትራ ባሕር በኋላቸው የፈርዖን ሰራዊት ሲያስጨንቃቸው አደረ ።አይ ያች ሌሊት ምን አይነት ሌሊት ናት? እነሱ ተጨነቁ እንጅ እግዚአብሔር ግን በደመና እየጠበቃቸው ነበር።ጎህ ሲቀድ እግዚአብሔር ተአምሩን ገለጠ ሙሴን ባሕሩን በተአምረኛው በትሩ እንዲመታው አዘዘው ሙሴም የታዘዘውን አደረገ ።እግዚአብሔርም ባሕሩን ከፈለ ዕብራውያንንም በሰላም ባሕርን ከፍሎ አሻገራቸው።ፈርዖንም እንደ ዕብራውያን እሻገራለሁ መስሎት ከነሠራዊቱ ወደባሕር መግባቱ አልቀረም።እግዚአብሔር ሁሉም እስኪገቡ ጠበቃቸው ።ዕብራውያን ከባሕር ሲወጡ ግብፃውያን ወደባሕር ሲገቡ ሙሴ ለሁለተኛ ጊዜ ባሕሩን በብትሩ መታ ባሕሩም ወደቀደመ ማንነቱ ተመለሰ ።ፈርዖንም ከነሰራዊቱ ውሃ ሆኖ ቀረ። የዕብራውያንን ልጆች በውሃ ያስጣለው ፈርዖን ራሱም በውሃ ሰጠመ ።ዕብራውያን በሰላም ተሻግረው አምላካቸውን አመሰገኑ ክፋተኞች ግን በክፋታቸው ሰጠሙ ።የክፋዎች መጨረሻቸው ስጥመት ነው ።የመልካሞች ግን ባሕርን ከፍሎ መሻገር ነው።እግዚአብሔር ሆይ እኛንም ከኀጢአት ባሕር ያሻግረን ዘንድ ሙሴን ላክልን።
መምህር መልአክ መሠለ
የአንዲዳ መድኃኔዓለም የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት
የትርጓሜ መምህር
