ኤክቱስ ጥር 10/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ ሁልጊዜ ከበዓለ ጥምቀት አንድ ቀን አስቀድሞ የሚከበረው እና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መውረዱ የሚያሰስብበት በዓል በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት በዲላ ከተማ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
በዕለቱ ታቦታቱ ከአድባራቱ ተነስተው በካህናትና በበርካታ ምዕመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባሕር ጉዞ አድርገዋል።
በበዓሉ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በዶክተር መስፍን ደምሴ ጋባዥነት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ በበዓሉ ተገኝተው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ንግግር ያደረጉ ሲሆን በዕለቱ በዓሉ በልዩ ሁኔታ እንዲከበር አስተዋጽዖ ላደረጉ አካላትና በዓሉን ከሚመሩት ሕዝብ ጋር በጋራ ለማክበር ለመጡ የመንግሥት አካላት ምሥጋና አቅርበው በጸሎት ፈጽመዋል።
በዕለቱ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ፣ የጌዴኦ ዞን እና የዲላ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጠበብት መሪጌታ መሰረት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በርካታ ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን ተገኝተዋል።
“ወአሜሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ ይጠመቅ እምዮሐንስ – ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ” ማቴ ፫፥፲፫

