በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ተጠምቀ ሰማያዊ በዕደ መሬታዊጥምቀት ከሰባቱ  ምሥጢራተ  ቤተክርስቲያን  አንዱ ነው፡፡

  የምሥጢረ ጥምቀት መሥራች ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ሲሆን በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ በፍጹም ትህትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ይህንንም ያደረገልን አብነት ሊሆነን ነው። ምክንያቱም ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስን “መጥተህ አጥምቀኝ” ብሎት ቢሆን ኖሮ ነገ ነገሥታቱና መኳንንቱ ካህናቱን “መጥታችሁ አጥምቁን” ባሉ ነበር። ስለዚህ እንዲህ እንዳይሆን ነው ጌታችን “ጌታ” ሲሆን በባሪያዬ እጅ እንደተጠመቅሁ እናንተም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዳችሁ በካህናት እጅ ተጠመቁ ሲል ነው። 

ቅደስ ዮሐንስ ጌታችን በእርሱ እጅ ለመጠመቅ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ “እኔ ባሪያህ በአንተ በጌታዬ እጅ ልጠመቅ ያስፈልገኛል እንጂ አንተ በእኔ በባሪያህ እጅ ትጠመቅ ዘንድ እንዴት ወደ እኔ ትመጣለህ?” አለው። ጌታችንም መልሶ “አሁንስ ፍቀድልኝ፣ እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና /ትንቢተ ነቢያትን እንዲህ ልንፈጽም ያስፈልጋል/” አለው። በዚህን ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን አጠመቀው። በዚህም “መጥምቀ መለኮት” ተብሎ የቅዱስ ዮሐንስ ገናንነቱ ይነገራል፣ ጌታችንም በባሪያው እጅ በመጠመቁ ፍጹም ትህትናው ይነገርለታል።
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በኃጢአት የተዳደፉት ሁሉ ንስሐ ገብተው የተዘጋጀላቸውን መንግሥት ወራሾች ይሆኑ ዘንድ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ ሲሰብክ ነበር። ይህ “መንግሥተ ሰማያት በልጅነት፤ ልጅነት ደግሞ በሃይማኖት ልትሰጥ ቀርባለችና ከኃጢአት ተለይታችሁ፣ ከበደል ርቃችሁ ቅረቡ” ማለት ነው። በነቢያት እንደተነገረውም “ የእግዚአብሔርን መንገድ አዘጋጁ፣ ጥርጊያውንም አቅኑ” እያለ ድምጹን አሰምቶ ሰብኳል። ምሥጢሩንም በመጣ ጊዜ ተራራውና ኮረበታው ተንዶ፣ ጎድጓዳው ተመልቶ፣ ሥሩ ተነቅሎ፣ ደንጊያው ተለቅሞ ለፈረስ ለሰረገላ እንዲመች ተደልድሎ እንደሚቆይ ሁሉ እናንተም የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን ሰውነታችሁን ከኃጢአታችሁ ንጹሕ አድርጋችሁ ጠብቁ ማለት ነው። 

ቅዱስ ዮሐንስ ከንስሐው ስብከት በተጨማሪም ዘመን የማይቆጠርለት ሲሆን ሥጋን በመለበሱ ዘመን ተቆጥሮለት ከእርሱ በኋላ ስድስት ወር ዘግይቶ ስለሚመጣው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትም ሰብኳል፦ “እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል። እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው። አውድማውንም ስንዴውንም በጎተረው ይከታል፤ ፈጽሞ ያጠራል፤ ሰንዴወንም በጎተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል። /ማቴ 3፡11፤ ዮሐ 1፡26/

ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢአት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው፡፡ ጥምቀት በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒያ በግእዝ አስተርዮ በአማርኛ መገለጥ ይባላል፡፡ ቃሉ በቀጥታ ሲተረጎም በውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣ መነከር፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው፡፡

ጌታችን ለምን ተጠመቀ?

የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ አዳምና ሔዋን ፍዳው በፀናባቸው መከራው በበዛባቸው ጊዜ የሚያቃልልላቸው መስሏቸው ዲያብሎሰ ስመ ግብርናችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ ባላቸው ጊዜ አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ (አዳም የዲያብሎስ የወንድ አገልጋይ) ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ (ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ) ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ዲያብሎስም ይህንን ደብዳቤ አንዱን በሲኦል አንዱን በዮርዳኖስ አስቀመጠው፡፡ በዮርዳኖስ ያስቀመጠውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ ደምስሶታል፡፡ ይህንን ጽሕፈት ለመደምሰስ ነው ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው” ያለው /ቆላ 2፥14/፡፡

ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ የላይኛው ሸሽቶ ወደ ላይ ተመልሶ ሽቅብ ፈሷል፡፡ የታቹም ወደ ታች ሸሽቷል፡፡ የላይኛው ፈሳሽ ተቋርጦ እንደ ክምር ተቆልሎ ቀርቷል።ቅዱስ ዳዊት የተመለከተውም ይህንኑ ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በዘር ይወርድ የነበረው ፍዳ መርገም በክርስቶስ ቤዛነት ተቋርጦ ፤ የታቹም ፈጽሞ መድረቁ ኃጢአተ አዳም የመጥፋቱ ምሳሌ ነው፡፡ እስራኤል ፈለገ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ መሔዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከኃጢአት ቍራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት ወደ ዕረፍት መንግሥተ ሰማያት አቅንተው ለመሔዳቸው ምሳሌ ነው፡፡ ኢያሱ የጌታ፣ እስራኤል የምእመናን፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ ምድረ ርስት የገነት መንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡

ምስጢረ ሥላሴን ለመግለጥ ጌታችን በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ ግልጽ ሆኗል፡፡ አብ በደመና “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑን ሲያስረዳ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ተቀመጠ ወልድም በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ፡፡ ስለዚህ ምሥጢርን ለመግለጥ ስንል የአንድነት የሦስትነት ምስጢር በጐላ ሁኔታ እንዲታወቅ ተጠመቀ ማለት ነው፡፡ /ማቴ. 3፥16/

ትንቢቱን ለመፈጸምአቤቱ ውሆች አዩህ፣ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ ውሆችም ጮኹ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ተጠመቀ /መዝ 77፥16/፡፡

              ወስብሐት ለእግዚአብሔር
           ሊቀትጉሃን ቀሲስ ሀብታሙ አበበ
      የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ

Scroll to Top