በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሁለት ሺህ አስራ ስምንት ዓመተ ምሕረትን በአተ ጾመ ፍልሰታን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት!

ኤክቱስ ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የምትገኙ፣ በሀገር ውስጥና በመላው ክፍላተ ዓለም የምትኖሩ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤ እንኳን ለሁለት ሺህ አስራ ስምንት ዓመተ ምሕረት ለበአተ ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ።

“ አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።” (መዝ. ፻፴፩፥፰)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካሉ ሰባት የአዋጅ አጽዋማት መካከል ይህ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ወደ ገነት መፍለሱንና በኋላም እንደ ልጇ ትንሣኤ መነሣቷን የምናስብበት ይህ ጾም አንዱ ነው።

ይህ ወቅት ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ለነፍስ በማስገዛት ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበትና መንፈሳዊ ሕይወታችንን የምናድስበት ታላቅ የሱባኤ ወቅት ነው።

ስለሆነም ይህንን የተቀደሰ የጾም ወቅት እያንዳንዱ ምዕመን በረከትን በሚያስገኝ መልኩ በሰዓታት፣ በኪዳን፣ በማኅሌት፣ በቅዳሴ፣ በውዳሴ ማርያምና በቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ እንዲሁም በሁሉም መንፈሳዊ አገልግሎት እንድታሳልፉ አባታዊ መመሪያችንን እናስተላልፋለን። ይልቁን በዚህ ወቅት ጾም ያለ ንስሐና ያለ ቅዱስ ቁርባን ሙሉ ሊሆን ስለማይችል ከዓለም ጫጫታ ርቀን ንሥሐ ገብተን የአምላካችንን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን ራሳችንን ለሰማያዊው መንግሥት በማዘጋጀት የምናሳልፍበት ሊሆን ይገባል።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
ይህ ወቅት እርስ በርስ የምንቀራረብበት የጥልን ግድግዳ የምናፈርስበትና ሰላምን የምንሰብክበት መሆን አለበት። አንዱ ለሌላው በመጸለይ የወንድማማችነት ፍቅርን ማሳየት ይኖርብናል። “ወአኮ ጾም እምኅብስት ወማይ አላ ጾምሰ ዘውኩፍ ቅድመ እግዚአብሔር ንጽሐ ልብ – ጾም ከእህል ከውሃ መከልከል ብቻ አይደለም እግዚአብሔር የሚቀበለው ጾም የልብ ንጽሕና ናት” እንዲል ፍት ነገ. አንቀጽ 15÷598  ከምግብ መከልከል ብቻ እውነተኛ ጾም ሊሆን ስለማይችል በንጹሕ ልብ ሆነን የተራቡትን በማብላት፣ የታረዙትን በማልበስና የተቸገሩትን በመርዳት መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ከሌለባት በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን እያማለደች ከምታሰጥ ከእመቤታችን ረድኤት በረከት የምንቀበልበት ጾም እንዲሆን አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ!

አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

Scroll to Top