በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው መንፈሳዊ ጉባኤ በብፁዕነታቸው ቡራኬ ተጠናቀቀ!

ኤክቱስ ሰኔ 22/2018 ዓ.ም

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በኮቾሬ ገደብና ጮርሶ ወረዳዎች ቤተ ክህነት በጨለለቅቱ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ዐቢይ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጠናቋል።

የጉባኤው ዋና ዓላማ ከቤተ ክርስቲያን የራቁ ምዕመናንን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ ለማድረግ ሲሆን በተጨማሪም የቅዱሳን ምሥጢራትን ሡታፌ ለማሳደግ ያለመ ነው።

በጉባኤው የተገኙት መምህራን ሊቀ ሊቃውንት ዮሴፍ ደሳለኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል፣ መጋቤ ሀዲስ አድነው ወንድሙ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ዙርያ ሰፊ ትምህርት ሲሰጡ ቆይተዋል። በተጨማሪም በዝማሬ ሙዐዘ ስብሐት ዳግማዊ ደርቤ፣ ዘማሪት ምርትነሽ ጥላሁንና ዘማሪ ጌታሁን ታደሰ (በጌዴኡፋ ቋንቋ) ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው በጉባኤው እጅግ መደሰታቸውን የገለጹ ሲሆን ከሩቅ ሀገር ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የመጡት መምህራንና ዘማርያንን፣ ይህንን ጉባኤ ያዘጋጁትን የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደርን በአጠቃላይ ተሳትፎ ያላቸውን አካላት በሙሉ አመስግነዋል።በተጨማሪም በጌዴኡፋ ቋንቋ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን አባታዊ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው በጸሎት ፈጽመዋል።

Scroll to Top