በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

የሀገረ ስብከት ቅድመ ታሪክ

የሀገረ ስብከት ቅድመ ታሪክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ ዐዋዲ ምዕራፍ ስድስት፣ ዐንቀጽ ሠላሳ ስምንት እስከ አርባ አምስት ድረስ በተዘረዘረው መሠረት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ጽ/ቤት ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር መሠረት የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት መሥርቶ እና አጠናክሮ መሥራቱ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው፡፡
በቃለ ዐዋዲው ዐንቀጽ አርባ ሦስት ቁጥር አንድ ላይ እንደ ተገለጠው «የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ገዳማት፣ አድባራት እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በየደረጃው ለተቋቋሙት ሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያትና ለወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ አመራርና ከፍተኛ የአስተዳደር ኃላፊነት ያለው መሥሪያ ቤት ነው»

በእንግሊዝኛው «ዳዮሰስ» የሚለው ቃል dioikesis ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው፡፡  በመሆኑም ሀገረ ስብከት ማለት በአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ አንድ አካባቢ ማለት ነው፡፡
ሀገረ ስብከት ለመጀመርያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው ቅዱሳን ሐዋርያት የጌታችንን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ ዓለምን ዕጣ በዕጣ ተከፋፍለው ለማስተማር በወጡ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ይመቻል፣ አይመችም ሳይሉ በተሠማሩበት ሀገረ ስብከት ገብተው አብያተ ክርስቲያናትን በመትከል፣ ምእመናንን አስተምረው በማጥመቅ፣ ካህናትን እና ዲያቆናትን በመሾም የወንጌልን ቃል ለዓለም አዳርሰዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሀገረ ስብከቱ፣ ዮሐንስ ወንጌላዊው በታናሽ እስያ ሀገረ ስብከቱ፣ ቶማስ በሕንድ ሀገረ ስብከቱ፣ማርቆስም በእስክንድርያ የሠሩት ሥራ ለዚህ ማስረጃችን ነው፡፡

በኢትዮጵያውያን ነገሥታት እና ሕዝብ በጎ ፈቃድ እና አርቆ አስተዋይነት ወደ እስክንድርያ ተልእኮ ለጵጵስና የበቃው የመጀመርያው ጳጳስ ፍሬምናጦስ ሀገረ ስብከት «ጳጳስ ዘአኩስም ወዘኩላ ኢትዮጵያ» የሚል ነበር፡፡ ከእርሱ በኋላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር እንደ አንድ ሀገረ ስብከት ሆና ከአንድ ሺ ዓመታት በላይ ቆይታለች፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በተለያዩ ጊዜያት ከአንድ በላይ ሊቃነ ጳጳሳት ተሾመው መጥተው ስለነበር ከአንድ በላይ አህጉረ ስብከት እንደነበራት ይጠቁማል፡፡ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በ1438 ዓም ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ከግብጹ ፓትርያርክ ዮሐንስ 14ኛ ተሾመው መጥተው ነበር፡፡ እነዚህ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ለአምሐራ፣ አቡነ ገብርኤልም ለሸዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው ተመደቡ፡፡ ይህም በወቅቱ የነበረውን የሀገረ ስብከት አደረጃጀት ያመለክታል፡፡

በዐፄ ዮሐንስ ጊዜም በ1874 ዓ.ም አራት ጳጳሳት ከግብጽ መጥተው አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ፣ አቡነ ማቴዎስ የሸዋ ጳጳስ፣ አቡነ ሉቃስ የጎጃም፣ አቡነ ማርቆስ የበጌምድር ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው ተሾመዋል፡፡ እነዚህ አበው በውል የተለየ ቦታ ተከልሎ ተሰጥቷቸው እንደነበር ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ በጻፉት «ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ» በተባለው መጽሐፋቸው የአቡነ ማቴዎስን ሀገረ ስብከት ሲዘረዝሩ «ሸዋን ከበሽሎ ወዲህ መደብ አድርገው የጁን፣ ዋድላን፣ ደላንታን፣ ዳውንትን፣ ግራ መቄትን፣ ከበጌምድር መጃን፣ ስዲን፣ ፎገራን፣ ጭህራን፣ደምቢያን፣ አርማጭሆን፣ መረባን፣ ጃን ፈቀራን፣ ጃንዋራን፣ ቆላ ወገራን፣ ጠገዴን፣ ወልቃይትን» እያለ ይዘረዝራል፡፡

በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ  ኃይለ ሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመርያዎቹን ጳጳሳት ስታገኝ የታወጀው ዐዋጅ ዐንቀጽ አንድ «የኢትዮጵያ የመላው ሊቀ ጳጳሳት በአቡነ ቄርሎስ ሆኖ ደቡቡ ለአቡነ ሳዊሮስ፣ ምዕራቡ ለአቡነ አብርሃም፣ ምሥራቁ ለአቡነ ጴጥሮስ፣ አዜቡ ለአቡነ ሚካኤል፣ ሰሜኑ ለአቡነ ይስሐቅ ይሁን» ይላል፡፡ ይኼው ዐዋጅ የየአንዳንዱን ጳጳስ የሀገረ ስብከት ክልል ዝርዝር እና የመንበረ ጵጵስናውን ማረፊያ ከተማ ይተነትናል፡፡

በጣልያን ዘመን ግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እና ጳጳሳት ተሰባስበው ብጹዕ አቡነ አብርሃምን ሊቀ ጳጳስ አድርገው አምስት ጳጳሳትን ሲሾሙ አዳዲስ አህጉረ ስብከት ተመሠረቱ፡፡ አቡነ ዮሐንስ የሸዋ፣ አቡነ ማርቆስ የኤርትራ፣ አቡነ ማቴዎስ የወሎ፣ አቡነ ገብርኤል የጎንደር እንዲሁም አቡነ ሉቃስ የወለጋ አህጉረ ስብከት ጳጳሳት ሆነው ተሾመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራስዋን አህጉረ ስብከት መመሥረት የጀመረችው ከራስዋ ልጆች መካከል ፓትርያርክ ባገኘች ጊዜ ነበር፡፡ በ1943 ዓም የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ አቡነ ታዴዎስን ለጎሬ፣ አቡነ ገብርኤልን ለወሎ፣ አቡነ ማርቆስን ለኤርትራ፣ አቡነ ፊልጶስን ለኢየሩሳሌም፣ አቡነ ጎርጎርዮስን ለከፋ ጳጳሳት አድርገው ሾመው ነበር፡፡ ይህም አዳዲስ አህጉረ ስብከት መመሥረታቸውን ያመለክታል፡፡ በ1948 ዓ.ም ትግራይ በሀገረ ስብከትነት ተቋቁሞ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ተሾመውበታል፡፡  በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአህጉረ ስብከት ቁጥር በየጊዜው እያደገ መጥቶ፣ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ» በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገለጡት፣ በ1974 ዓ.ም የአህጉረ ስብከቱ ዕድገት ወደ አሥራ ዘጠኋ ያህል ደርሶ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም» የተሰኘው  የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መጽሐፍ እንደሚገልጠው አርባ በሀገር ውስጥ፣ ስምንት ከሀገር ውጭ፤ በድምሩ አርባ ስምንት አህጉረ ስብከት ይገኛሉ፡፡

ሀገረ ስብከት ሀገረ ስብከት ቤተ ክህነቱን ወክሎ የሚሠራ ተቋም ሲሆን፣ ሃይማኖቱን እና ቀኖናውን ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ፣ ከክርስቶስ ጀምሮ የመጣውን ሀብተ ክህነት ለመጠበቅ እና ለማስተላለፍ፣ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፣ ገዳማት እና አድባራት እንዲረዱ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲተከሉ፣ ምእመናን ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መብት እንዲከበር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ወጥ እና ሥርዓቱን የጠበቀ እንዲሆን፣ የካህናት አስተዳደር እና አገልግሎት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት እንዲሆን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት እና ንብረት በሕግ እና በሥርዓት መሠረት እንዲጠበቅ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እና እንዲሰጡ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ተግባሮቹ ናቸው፡፡

  1. ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የምትጓዘው ሐዋርያት በተጓዙበት መንገድ ነው፤ ሥርዓቷም ትወፊቷም፣ አሠራርዋም ሐዋርያዊ ነው፡፡ አባቶቻችን ሐዋርያት ወንጌል ሰብከው ሃይማኖት ያስፋፉት አህጉረ ስብከትን እየመሠረቱ በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ባለበት ሁሉ ሀገረ ስብከትን መመሥረት እና ማጠናከር ሃይማኖታዊ ግዴታ በመሆኑ ነው፡፡
  2. የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት በወጥነት ለማስጠበቅ፡  የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ሥርዓት እና ትውፊት ወጥ በሆነ መልኩ ሊጠበቅ የሚችለው አንድ ወጥ የሆነ የማስጠበቂያ መንገድ ሲኖራትና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን፤ ልዩ ልዩ ተቋማትን፤ ካህናትና ምእመናንን በአንድነት ማስተባበር አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡
  3. የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን አንድነት እና ትብብር ለማጠናከር፡— በአዲስ አበባ የሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት  ከሀገረ ስብከቱ መመሪያ በመቀበልናበመመካከር  የተመሠረቱ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በመካከላቸው የሚኖረውን ግንኙነት የሚያስተባበር፣ እንዲረዳዱ፤ እንዲተባበሩ እና ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በጋራ እንዲሠሩ የሚያደርግ ማዕከላዊ አካል አስፈላጊ በመሆኑ  ነው፡፡
  4. ቤተ ክርስቲያን ለምታደርገው ኢኮኖሚካል ግንኙነት መንገድ ለመጥረግ፡- በአኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለሚደረገው ሃይማኖታዊ  ግንኙነት፣ ከሌሎች ጋር ለሚደረገው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ ሲኖዶስን ወክለው መሥራት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ግንኙነቱ በሊቀ ጳጳስ ደረጃ መደረግ ያአለበት በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ግንኙነት መልከ ለማስያዝ፣ ደረጃውን ለማስጠበቅና ውጤታማ ለማድረግ   የተጠናከረ እና ከሌሎች በእኩልነት የተደራጀ  ሀገረ ስብከት ያስፈልገናል፡፡
  5. በገጠርና በከተማ የሚገኙ ገዳማት እና አድባራትን በተጠናከረ መንገድ ለመርዳት፡- በችግር ላይ ያሉትን ገዳማት እና አድባራት በተበታተነ መንገድ ሳይሆን አንድ ወጥ እና ውጤት ሊያመጣ በሚችል መንገድ ለመርዳት እንዲቻል በማዕከላዊነት የሚያስተባበር እና የሚከታተል አካል ያስፈልገናል፡፡ ይህ አካል በሀገረ ስብከቱ ያለውን አስተዋጽዖ የሚያስተባብር፣  ሠንሠለቱን ጠብቆ ከመንበረ ፓትርያርኩ ጋር በመገናኘት ሥራው እንዲፈጸም የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና መሠረት ጉዳዩ የሚመለከተው በሀገረ ስብከት ደረጃ ነው፡፡
  6. ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለማስተባበር፡—  አንድነትን ለማምጣት እና ተባብሮ ለቤተ ክርስቲያን ለማገልገል በማሰብ የተደራጁ አያሌ ማኅበራት፣ ተቋማት እና በጎ ፈቃደኞች  ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራት እና አንድነቶች ከአጥቢያዎች ዐቅም እና ወሰን በላይ በመሆናቸው ላቅ ያለ አስተባባሪ እና አጋዥ አካል ያስፈልጋቸዋል፡፡ የእነዚህ ማኅበራት እና አንድነቶች አገልግሎት የተቃና፣ የተሳካ እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ደግሞ ከሀገረ ስብከቱ የተሻለ መዋቅር አይገኝም፡፡ ሀገረ ስብከቱ ተደራጅቶ የአገልግሎት መሥመሩን በሚገባ ካልዘረጋ በቀር የእነዚህ ማኅበራት እና አንድነቶች አገልግሎት ዝርው ይሆናል፡፡ ከዋናው ግንድ የተለየ ቅርንጫፍ ነውና፡፡
  7. ኢትዮጵያውያን  የሆኑ ወገኖችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማቅረብ፡—  ኢትዮጵያውያን የሆኑና ያልሆኑ ወገኖች ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርበው፤ ወንጌል ተምረው፣ አምነው እና ተጠምቀው የዚህች ቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዲሆኑ ማድረግ አንዱ ኃላፊነታችን ነው፡፡ የእነዚህ ወገኖቻችን ሱታፌ ደግሞ በማመን እና በመጠመቅ ማብቃት የለበትም፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ነባር ትምህርት ተምረው አሠረ ክህነቱንም መከተል አለባቸው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ከገዳማት አድባራት፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ት/ቤቶች እንዲሁም ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚያገናኛቸው አካል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሀገረ ስብከቱ መጠናከር ወሳኝ ነው፡፡
  8. ገዳማት እና ማሠልጠኛዎችን ለማቋቋም እና ለመምራት፡—  አዲሱ ትውልድ ከገዳማዊ ሕይወት እና ሥርዓት ጋር እንዲተዋወቅ፣ ምእመናን ሱባኤ እንዲይዙበት፣ ጠበል ለመጠመቅ፣ ጸሎት ለማድረግ እና ከዚህ ዓለም ጭንቀት ራስን ለመፈወስ የሚያስችሉ ገዳማትን በምንኖርበት ዓለም ለመመሥረት እና ለማስተዳደር፣ ከዚያውም ጋር አያይዞ ማሠልጠኛዎችን በማቋቋም ካህናትን፣ ዲያቆናትን እና መምህራነ ወንጌልን ለማፍራት የበላይ ሆኖ የሚከታተለውና ሥርዓቱን የሚያስጠብቀው ሀገረ ስብከት ቀድሞ መደራጀት ይገባዋል፡፡
Scroll to Top
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት