በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ ኢሳ 6÷6

ቃሉን የተናገረው ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ነቢዩ ኢሳይያስ ነው
የስሙም ትርጓሜ “መድኃኒት” ማለት ነው፡፡ ሆሴዕ፣ ኢያሱ፣ ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት እንደኾነ መድኃኒት መባሉ ግን እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ ባጭር ታጥቆ፥ ጋሻ ነጥቆ፥ ዘገር ነቅንቆ አማሌቃውያንን አጥፍቶ እስራኤልን አድኖ፥ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዉን ቆርሶ፥ ደሙን አፍስሶ፥ 13ቱን ሕማማተ መስቀል ታግሦ፥ አጋንንትን ድል ነስቶ ነፍሳትን አድኖ አይደለም፤ ተልእኮውን የሚገልጥ ነው እንጂ፡፡ በሌላ አገላለጽ ሊመጣ ያለው መሲሕ ማለትም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግልና ተፀንሶ፣ በድንግልና ተወልዶ፣ ቀስ በቀስ አድጎ፣ የደቂቀ አዳምን ሕማም ተሸክሞ አጠቃላይ የሰው ልጆችን በአስደናቂ መጎብኘትን ጎብኝቶ እንደሚያድናቸው ስለሚናገር “ኢሳይያስ – መድኃኒት” የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡
አባቱ አሞጽ እናቱ ደግሞ ሶፍያ ይባላሉ።
ነቢዩ ኢሳይያስ በኢየሩሳሌም ሲኖር በአካዝና በሕዝያስ ዘመነ መንግሥት የቤተ መንግሥት አማካሪ ነበር፡፡ በራሱ መጽሐፍ እንደነገረንም በዘመኑ የነበሩ የይሁዳ ነገሥታት ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ ይባላሉ /ኢሳ.1÷1/የነቢይነትን ሥራ የዠመረውም ወዳጁ ዖዝያን በሞተ በዓመቱ ነው፡፡ ይኸውም በ740 ዓ.ዓ. አከባቢ ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “ዖዝያንን ገስጽ” ሲባል ወዳጁ ስለኾነ ይሉኝታ ይዞት እምቢ ብሎ ነበር፡፡ ከዚኽም የተነሣ ከአፉ ላይ ለምፅ ወጣበት፡፡ ጌታም ተገልጦ፡- “የምትወደውና የምታከብረው ዖዝያን ሞተ፤ መንግሥቱም አለፈ፡፡ ሞት፣ ኅልፈት፣ በመንግሥቴም ሽረት የሌለብኝ እኔ አምላክኽ ብቻ ነኝ” አለው፡፡ ኢሳይያስ ይኽን ሲሰማ እጅግ ደነገጠ፡፡ ዳግመኛም እግዚአብሔር፡- “ወደዚኽ ሕዝብ ማንን ልላክ?” አለው፡፡ ኢሳይያስም፡- “እኔ እሔድ ነበር፤ ግን በአፌ ለምፅ አለብኝ” ሲል መልአኩ በጉጠት አፉን ቀባውና ለምፁ ድኖለት ትንቢት ተናግሯል ። “ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ” ኢሳ 6÷6  ያለውም ለዚህ ነው።

እግዚአብሔር አምላካችን ሃያ አራት ሊቃነ መላእክትን መርጦ በመንበረ መንግሥት ዙሪያ ክንፍ ለክንፍ አያይዞ አቁሟቸዋል፡፡ የብርሃን ዘውድ (አክሊል) ደፍቶላቸዋል፡፡ የብርሃን መስቀልና ማዕጠንተ ወርቅ አስይዟቸዋል፡፡ እንደዚህ አድርጎ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ እንዲያመሰግኑት አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህም ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ይባላሉ፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ እንደምናገኘው በየዓመቱ ኅዳር 24 ቀን በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው ሰማያዊ አገልግሎት የሚሰጡ የካህናተ ሰማይ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ስለ ካህናተ ሰማይ አገልግሎት የሚያስገነዝብ አጭር ትምህርት እንማማራለን።

ሱራፊ ማለት መልአክ፣ ከካህናተ ሰማይ አንዱ ማለት ነው፡፡ ሱራፌን፣ ሱራፌል፣ ሱራፌም (በፅርዕ ሴራፊም፣ በዕብራይስጥ ስራፊም) ማለት የነገድ ስም፣ ልዑላን መላእክት፣ ሊቃናት፣ የሚያጥኑ፣ ካህናት፣ ቀሳውስት፣ ቀዳሾች ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፰፻፹፮/፡፡ ከዚህ ላይ ሱራፊ ነጠላ ቍጥርን፤ ሱራፌል ደግሞ ብዙ ቍጥርን ያመለክታል፡፡ ሱራፌል ለቅዱሳን በሰው አምሳል በመገለጣቸው ሽማግሌዎች ተብለው ተጠርተዋል /ኢሳ.24፥23፤ መሳ.13፥2 ፤ ዳን.10፥18/፡፡ በግእዝ ቋንቋ ደግሞ ካህናተ ሰማይ ይባላሉ፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው የሚሰጡትን ሰማያዊ አገልግሎት የሚያመለክት ስም ነው፡፡

ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ ‹‹በዙሪያውም ሃያ ዐራት ካህናት አሉ፡፡ በፊታቸው የበጉን ሥዕል፣ ደምን የተረጨች ልብስንም፣ የታተመ መጽሐፍንም ያያሉ፡፡ መንበሩን በዞሩ ቍጥር ለዚያ ለበጉ ሥዕልና በደም ለታለለችዋ ልብስ፣ ለታተመው መጽሐፍም ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› /ራእ. 4፥6 ፤5፥8/ በማለት ስለ ሱራፌል ሰማያዊ አገልግሎት የተናገረ ሲኾን፣ ‹‹በፊታቸው የበጉን ሥዕል ያያሉ›› ማለቱ የክርስቶስን ትስብእት በጌትነት ያዩታል ለማለት ነው፡፡ ‹‹ወደቁ›› ሲልም መስገዳቸውን ያመለክታል፡፡ ‹‹በግ›› የተባለውም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ደምን የተረጨች ልብስ›› ማለቱም ክርስቶስ ስለ እኛ መከራ መቀበሉን፤ የታተመ መጽሐፍ የክርስቶስ ትስብእት የማይመረመር መኾኑን፤ ‹‹ለበጉ ሥዕል፣ ለታለለችው ልብስና ለታለለው መጽሐፍ ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› ሲልም ከእግዚአብሔር አብ እና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነትም በሦስትነትም ለሚመለከው ለክርስቶስ ደግመው ደጋግመው ምስጋና ማቅረባቸውንና መገዛታቸውን ያመለክታል /የሠለስቱ ምእት ቅዳሴ አንድምታ ትርጓሜ፣ 3፥7-9/፡፡

ነቢዩ ሕዝቅኤልም ካህናተ ሰማይ ያለ ዘር መገኘታቸውን ሲያመለክት ‹‹በመንበሩ ዙሪያ ቁመው ያሉ ካህናት ኅብራቸው መረግድ የሚባል ዕንቍን ይመስላል›› በማለት ተናግሯል፡፡ ጸጋቸውን ሲገልጽ ደግሞ ‹‹ብሩህ ልብስ ለብሰዋል፤›› ክብራቸውን ሲመሰክርም ‹‹በራሳቸው ላይ አክሊል ደፍተዋል›› ብሏል፡፡ ነጭ ልብስ ለብሰው መታየታቸው የንጽሕናቸውና የቅድስናቸው መገለጫ ሲኾን፣ በራሳቸው ላይ የተቀዳጁት ዘውድ ደግሞ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸውን ዘለዓለማዊ ክብር ያሳያል፡፡ ቍጥራቸው በሃያ አራት መገለጹም ምስጋናቸው ዕረፍታቸው፣ ዕረፍታቸው ምስጋናቸው ኾኗቸው ለሃያ አራት ሰዓታት ሳያቋርጡ ጸሎትና ምስጋናን ለእግዚአብሔር ማቅረባቸውን ለማጠየቅ ነው፡፡

ካህናተ ሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ሲያቀርቡ አክሊሎቻቸውን ከራሳቸው ላይ አውርደው ያለማቋረጥ ይሰግዳሉ፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ይህንን ሰማያዊ ሥርዓት እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፤ ‹‹ካህናተ ሰማይ ቅዉማን በዐውዱ አክሊላቲሆሙ ያወርዱ ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ ይርዕዱ ወኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ፤ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) በመንበሩ ዙሪያ ቆመው በፊቱ ሲሰግዱ የመለኮት እሳት ሲበርቅ እንዳይመታቸው ይንቀጠቀጣሉ፤›› /መጽሐፈ ሰዓታት/፡፡ ይህም ምስጋና በቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ የጸሎት ክፍሎች ይገኛል፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ አለ ፤ ቅዱሳን መላእክት  ለመራዳት፣ ለመጠበቅ፣ ለመታደግ ፣ ከተፍገመገምንበት ለማንሳት ፈጥነው ደራሽ መሆናቸውን ሲነግረን ነው ። እለ ስድስቱ ክነፊሆሙ ይላቸዋል ። ልዑል እግዚአብሔር የሰጣቸው ፀጋ ብዙ መሆኑን ሲያሰረዳን ነው ።
በእውነት ከሱራፌል አንዱ እየበረረ መጥቶ በጦርነት ለምጽ የተመታችውን ሀገራችነን ይፈውስልን ። የ24ቱ ከህናተ ሰማይ በረከታቸው ረድኤታቸው ይደርብን ይዋልብን ።

መልአከ ሰላም አምሳሉ ሳለ
የዲላ መካነ ቅድስት ሥላሴ ወአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ
ኅዳር 24/2018 ዓ.ም

Scroll to Top