በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

Uncategorized

በአርሲ ለተገደሉ ምዕመናን ጸሎተ ምሕላ ተደረገ!!

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በአንዲዳ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ ስቅለቱ እንደተከበረ ከዚህ በፊት በነበረ ዘገባ መግለጻችን ይታወቃል። በመርሃግብሩ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በኦርቶዶክሳውያን ላይ በተደረገው ጥቃት በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መመሪያ ሰጪነት እግዚአብሔር አምላክ የሞቱትን ነፍስ እንዲምርና በሀገሪቱ ላይ የመጣውን መቅሰፍት በምሕረቱ እንዲመልስ ጸሎተ ምሕላ ተደርጓል። በተጨማሪም ብፁዕነታቸው በአከባቢው የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት የአከባቢውን ሰላም ማስከበር ቀዳሚ ተግባራቸው እንደሆነ በአጽንዖት ገልጸዋል።

በአርሲ ለተገደሉ ምዕመናን ጸሎተ ምሕላ ተደረገ!! Read More »

“ሰፍሐ እደዊሁ ለሕማም – እጆቹን ለሕማም ዘረጋ”  ቅዳሴ ሐዋርያት

እንኳን ለመድኃኔዓለም ጥንተ ስቅለት በዓል አደረሰን አደረሳችሁ! Your Attractive Heading Your Attractive Heading የዛሬው በዓላችንን የምናከብርበት ምክንያት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የገለጠው አንድያ ልጁን ወደ ምድር ልኮ በተቀበላቸው ጸዋትወ መከራን በማሰብ ነው። የመጨረሻ ፍቅሩንም ያሳየው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቶ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን መከራን ተቀበለ? እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከመፍጠሩ በፊት ለሰው የሚያስፈልገውን እንዳይቸገር ሁሉን አመቻችቶ (አዘጋጅቶ) በስድስተኛው ቀን ዐርብ ዕለት በእርሱ መልክና አርአያ ፈጠረው በምድርም ላይ ለሚኖሩ ፍጥረታት ገዢ አድርጎ ከጎኑም አጥንትን ወስዶ ሔዋንን ፈጠረለት። አዳምና ሔዋን በገነት መካከል ያሉትን ፍሬዎች እንዲበሉ ፈቀደላቸው ነገር ግን ዕፀ በለስ የተባለችውን ፍሬ እንዳይበሉ አዘዛቸው ከዚህች ፍሬ ብትበሉ የሞት ሞትን እንደሚሞቱ አስጠነቀቃቸው። አዳምና ሔዋን ግን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ አክብረው መኖር የቻሉት ለሰባት ዓመታት ብቻ ነበር ሰይጣን ዲያብሎስ በእባብ ገላ አድሮ ወደሔዋን በመሄድ ከንቱ የሆነ ውዳሴን ለሔዋን በማቅረብ “ዕፀ በለሱን አትብሉ ያላችሁ እግዚአብሔር አምላክ እንዳትሆኑ ብሎ ነው ስለዚህ ከዕፀ በለሱ ብትበሉ አምላክ ትሆናላችሁ” ብሎ ሔዋንን ዕፀ በለሱን እንድትበላ የሐሰት ስብከትን ሰበካት ሔዋንም ቀጥፋ የዲያብሎስን ምክር ሰምታ ከአዳም ጋር በሉ። በበሉም ጊዜ ጸጋቸው ተገፈፈ ፍርሃትም ወደቀባቸው እግዚአብሔርም ከእነርሱ ተለየአዳምና ሔዋንም በእግረ አጋንት በኃጢአት ወድቀው ከክብር ተዋርደው በለስን በልተው ሞትን ሸምተው ለብዙ ዘመናት በጨለማ፣በፍርሃት፣የብርሃን ጸጋቸው ተገፎ በሐዘን ውስጥ ስንሰቃዩ እግዚአብሔርም ተመልክቶ   ተገለጠላቸውና አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው ብሎ ቃል ኪዳን ለአዳም ገባለት።በዚህም ጌታችን ሞታችንን ወስዶ ሕይወት ሊሰጠን መድኃኒት ልጁን ላከልን። “ፈነወ ለነ መዝራእቶ ልዑለ – ልዑል ክንዱን ሰደደልን” እንዳለ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬምበተጨማሪም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደላከው እንመሰክራለን” 1ኛ ዮሐ 4፥14 በዚሁ መሠረት ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት ወረደ ተወለደ ይኸውም ለአዳም ልጆች በሙሉ ለበደልነው፣ ለወንጀለኞች፣ ሕጉን ለጣስነው፣ በጨለማ ውስጥ ላለነው ፣ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ሲዖል እንድንወርድ ተፈርዶብን ለነበረው ፣ በእግረ ዲያብሎስ ስንረገጥ ለነበርነው እና ምንም የሚወደድ ማንነት የሌለን ስንሆን “እግዚአብሔር አንዲያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።ዮሐ 3፥16   ለኛ ሲል ምን ምን መከራን ተቀበለ? “የወልድን መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው? ምን ከንፈር ነው? ምን አንደበት ነው? የፍቁር የጌታ ሕማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያያል ሕሊናም ይመታል ነፍስም ትንቀጠቀጣለች ሥጋም ይደክማል” 1ኛ ከሊቶስትራ እስከ ቀራንዮ ከጲላጦስ አደባባይ እስከ ቀያፋ ጊቢ በአይሁድ በሊቃነ ካሕናት እጅ ተሰቃየ፣ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ጊዜ በጅራፍ ተገረፈ፣ አንድ መቶ ሃያ ጊዜ በጥፊ ተመታ፣ ሰማንያ ጊዜ ጺሙን ነጩት፣ ሰባ ሁለት ጊዜ አፉን በጡጫ መቱት፣ ሦስት መቶ የሚሆኑ ረዣዥም የእሾህ አክሊል በራሱ ደፉበት፣ ምራቅ ተፉበት፣ መስቀል ተሸክሞ እየወደቀ እየተነሳ ተሰቃየ።“እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ ስለበደላችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን።” ኢሳ 53 ፥7 እንዲሁም ጌታችን ስድስት ሰዓት ሲሆን አዳምና ሔዋን አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስ የበሉት በዚህ ሰዓት ነበረና ይህንን ለመካስ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ። ጌታችን በመስቀል እያለ ተአምራት ተፈጽመዋል በሰማይና በምድር 1ኛ ጸሐይ ጨለመ2ኛ ጨረቃ ደም ለበሰች3ኛ ከዋክብት ረገፉ         # በምድር1ኛ መቃብራት ተከፍተው ከ500 በላይ የሚሆኑ ሙታን ተነሱ2ኛ ድንጋዮች ተሰነጣጠቁ3ኛ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለ2 ተከፈለ4ኛ ዓለም ሁሉ ጨለማ ሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እያለ 13ቱን ህማማተ መስቀል ተቀብሏል። ጌታችን በመስቀል ላይ እያለ “ተጠማሁ “ሲል አንጀት የሚበጥስ ሀሞትና ከርቤ ቀላቅለው አጠጡት ሁሉን የሚያጠግበውን አጠጥቶ የሚያረካውን ተጠማሁ አለ። 40 ቀንና 40ሌሊት በጌቴሴማኒ  የጾመ ጌታ በአይሁድ እጅ 18 ሰዓታት ሳይሞላ ተጠማሁ ያላቸው ለምን ይሆን? ፍቅርን ሲገልጽ ነው አይሁድ ከታላቁ እስከ ታናሹ ድረስ በጠላትነት ተነስተውበታልና ለዚህም ነው ተጠማሁ ፍቅር ተራብኩ ሲል ነው።      ይህን ፍቅር የሆነውን ጌታ እስከመስቀሉ ያልተለዩ ሁለቱ ብቻ ነበሩ 1ኛ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የሚደርስበትን መከራ እስከ ቀራንዮ እየተከተለ መከራውን ፣ስቃዩን፣ መንገላታቱን ግርፋቱን አይሁድን ሳይፈራ ያይ ነበር ወንጌላዊው ቅ/ዮሐንስ ጌታ ይወደው የተባለው ቁጽረ ገጽ (ፊቱ በሐዘን) የሞላ የተባለው ለዚህም ነው በመጨረሻም በመስቀል እያለ እናቱን እነኋት እናትህ ብሎ በአደራነት የሰጠው2ኛ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት እርሷም የአይሁድን ዛቻ ዱላ ሳትፈራ እስከ ቀራንዮ የተከተለች በውስጧ እያለቀሰች ያ ሁሉ ስቃይ ሲደርስበት መጨረሻውን ሳላይ የትም አልሄድም ብላ መስቀሉ ስር የተገኘች ለመዳናችን ምክንያት የሆነች ንጽሕት፣ቅድስት፣ድንግል ለሁላችን የተሰጠች እናት ናት።    ስለዚህ የተከፈለልንን ውለታ በማሰብ በሕይወት ልንኖር ይገባል። 1ኛ በፍቅር ልንመላለስ ይገባል።         እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት    ዮሐ 15፥12ጠላቶቹ ሳለን ከወደደን     1ኛ 4፥16 እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል እግዚአብሔር ፍቅር ነው በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል።2ኛ በትህትና ሕይወት ልንኖር ይገባልእርሱን ሲንቁት አልናቃቸውም ሲታበዩበት በትህትና ያያቸው ነበር።    ሉቃ 23፥34    አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለእኛም ሰዎች ሲንቁን ሲታበዩብን በዝምታ በፍቅር ልናሳልፍ ይገባል። 3ኛ በትዕግስት ፦ እርሱ ሲሰድቡት  አልተሳደበም፣ በፈጠራቸው ፍጥረታት ምራቅ ተተፋበት ምንም መልስ አይሰጣቸውም ነበር በትዕግስት ይመለከታቸው ነበር እንጂ           2ጴጥ 3፥15 የጌታችንም ትዕግስት መዳናችሁ እንደሆነ ቁጠሩ4ኛ ሮሜ6፥5       ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ  ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን                     ጌታችን ከቤተልሔም ጀምሮ ብርዱ፣ የግብጽ ስደቱ፣ረሃቡ ጥማቱ ከሐሙስ ማታ 3፡00 እስከ ዐርብ 9፡00 የተቀበላቸው መከራዎች ለሰው ልጅ ነውእኛም የእርሱ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ስንሆን የሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራ አለ ነገር ግን የኛ አምላክ በመስቀል ተሰቅሎ በአዲስ መቃብር ተቀብሮ መቃብር ሊይዘው ሳይችል መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በራሱ ኃይልና ሥልጣን ሞትን ድል አድርጎ አሸንፎ ተነስቷል እኛም በእምነት ጸንተን ንስሐ ገብተን በመስቀል ላይ የቆረሰውን ቅዱስ ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን መንግስቱን እንድንወርስ ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም እንድንኖር አምላካችን ይርዳን።       ስብሐት ለእግዚአብሔር! መምህር በየነ ክፍሌየጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከትቁጥጥርና የምግባረ ሰናይ ክፍል ኃላፊ

“ሰፍሐ እደዊሁ ለሕማም – እጆቹን ለሕማም ዘረጋ”  ቅዳሴ ሐዋርያት Read More »

“የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ…ወንጌላዊ ።”ቆላስይስ 4፥14

ሉቃስ ማለት በላቲኑ ትርጓሜ ብርሃናማ፣ ብርሃን የያዘ ማለት ነው፡፡ በትርጓሜ ወንጌል የተሰጠው ትርጉም ደግሞ ሉቃስ ማለት ዓቃቤ ሥራይ (ባለ መድኃኒት) ማለት ነው፣ ቀድሞ ዓቃቤ ሥራይ ዘሥጋ (ሥጋዊ ሐኪም) ነበር በኋላ ግን ዓቃቤ ሥራይ ዘነፍስ ( መንፈሳዊ ሐኪም) ሆኗልና፡፡ አንድም ተንሣኢ (ፈጣን) ማለት ነው ለስብከተ ወንጌል ይፋጠናልና፣ አንድም መበሥር (ብሥራት ነጋሪ) ማለት ነው ብሥራተ መልአክን ይጽፋልና በማለት ይተረጉመዋል፡፡የተወለደው በሶርያ አንጾኪያ ነው፡፡አስቀድሞ ከ72ቱ አርድእት ወገን የተቆጠረ ሲሆን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወርዶ ወንጌልን ሰብኳል ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎሰ ጋር የተገናኘውም በዚሁ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ የሕክምና ሙያ የነበረው ሲሆን ያጠናውም ከአቴናና እስክንድርያ ሊቃውንት መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህ ሙያው በተጨማሪ የሥነ ሥዕል ችሎታም እንደነበረው ይነገራል፡፡ ይህንን ችሎታውንም በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ባለው ሥዕላዊ አገላለጥ ከማንጸባረቁም ሌላ በእጁ የተሳሉ ሥዕሎች በተለያዩ ሀገሮች ይገኛሉ፡፡የቅዱስ ሉቃስ ስዕሎች እመቤታችን ልጇን አቅፋ ( ምስለ ፍቁር ወልዳ) የሳላቸው ሲሆኑ በኢትዮጵያ በተድባበ ማርያም ፤ በደብረ ዘመዶ ፤ በዋሸራ ፤በጅበላ ሲገኙ ተመሳሳዩም በስፔን ቅድስት ማርያም ካቴድራል እንደሚገኝ ይነገራል ፡፡ የቅዱስ ሉቃስ ወንጌልየቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተጻፈው በሀገር አኪይያ (ሮም) በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ነው፤ የሉቃስ ወንጌል ‹የአሕዛብ ወንጌል›፣ ‹ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ›፣ ‹ሰባኬ ጸሎት›፣ ወንጌለ አንስት ተብሎም ይጠራል፡፡፩. ‹የአሕዛብ ወንጌል› እየተባለ የሚጠራው ወንጌሉ የተጻፈው ለአሕዛብ በመሆኑ ነው፡፡፪. ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ የሚባለው ስለ መንፈስ ቅዱስ ደጋግሞ ስለሚናገር ነው፡፡፫. ሰባኬ ጸሎት የተባለው ከሌሎች ወንጌላት የበለጠ ደጋግሞ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ጸሎት ጽፏልና ነው፡፡፬. ወንጌለ አንስት የሚባለው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ስለ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ ስለ ማርያም እንተ እፍረት፣ ስለ ናይን እና ወዘተ በስፋት ስለሚናገር ነው፡፡ወንጌሉን ከመጻፉ አስቀድሞም ቅዱስ ሉቃስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ትርጓሜ ወንጌል ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በአንጾኪያ ሀገር ቅዱስ ጳውሎስን ካገኘው በኋላም ሊቀ ሐዋርያው ሰማዕት እስከሆነበት ድረስ አገልግሎታል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ጋርም በነበረበት ጊዜም መቄዶንያ የምትባል ሀገር ከፍሎ እንዲስተምር እንደሰጠው በወንጌል ትርጓሜ ተገልጿል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም በዚያ ሀገር ከጌታችን ኢየሱስ መፀነስ ጀምሮ፣ መዋዕለ ስብከቱን፣ የሠራውን ትሩፋትና ገቢረ ተአምሩን በሙሉ ለአሕዛቡ በነገራቸው ጊዜ ከኃጢያት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ተመለሰው በማመን የክርስትና ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ ለስብከት በሚጓዝበትም ወቅት ትምህርት ባልተዳረሰባቸው ስፍራ ሲያስተምር አንድ ታዖፊላ የተባለ የእስክንድርያ መኮንን ስብከቱን አድምጦ በማመን ‹ዜና ሐዋርያትን› (ገድለ ሐዋርያትን) እንዲጽፍለት በጠየቀው መሠረት ጽፎለታል፡፡ በዚህም ቅዱስ ሉቃስ የጻፋቸው መጻሕፍት ከወንጌሉና ከሐዋርያት ሥራ ጋር ሦስት ናቸው፡፡ የሐዋርያት ሥራየሐዋርያት ሥራን የጻፈው ቅዱስ ሉቃስ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ከ1-34 ዓ.ም. ያለውን የክርስትና ታሪክ ካሰፈረ በኋላ ቀጣዩንና ከ34-58 ዓ.ም. ያለውን ደግሞ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ጽፏል፡፡ከምዕራፍ 1-8 ያለው የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በኢየሩሳሌም የሚያሳይ ሲሆን ከምዕራፍ 9-12 ያለው ታሪክ ደግሞ በእስጢፋኖስ ሰማኝትነት በተነሣው ስደት የተበተኑት የኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ልጆች በአካባቢው ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ የሚያሳይ ነው፡፡ ከምዕራፍ 13 ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስን ጉዞዎች ተከትሎ የጻፈውና ክርስተና በታናሿ እኪያር በአውሮፓ እንዴት እንደተሰበከ የሚያሳየው ክፍል ነው፡፡የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያው የሮም እሥራቱ በቁም እሥር ላይ ሆኖ ወንጌልን እንዲሰብክ ተፈቅዶለት በነበረ ሰዓት በሮም ከሚኖሩ አይሁድ ጋር በ58 ዓ.ም ስለሃይማኖት ያደረገውን ውይይት ተርኮ ያጠናቅቃል፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን የጻፈው በ58/በ59 ዓ.ም/ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ዓመተ ምሕረት በኋላ የተከናወኑትን ለምሳሌ በ60 ዓ.ም የቅዱስ ጳውሎስን መፈታት ዘግይቶም በ64 ዓ.ም. የደረሰውን የሮማ መቃጠልና የአይሁድን ዓመፅ በመጽሐፉ ስላልገለጠው ነው፡፡ቅዱስ ሉቃሰ ሐዋርያው ጳውሎስን ተከትሎ ታሪኩን ሲያሰባስብ ከኖረ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ ሲታሠር ዕረፍት በማግኘቱ አጠናቅሮ በመጽሐፍ መልክ በማዘጋጀት ለቴዎፍሎስ ልኮለታል፡፡ሉቃሰ ዘላሕም፡- አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ቅዱስ ሉቃስ ለምን በላም እንሚመሰል ሲናገር፣ የመድኃኒታችንን መሥዋዕትነት ሐዲስዋ እምቦሳ በወለደች በንጹሕ ላም ፍሪዳ መስሎ ይናገራልና ይለዋል፡፡ እንዲሁም በከብቶች በረት መወለዱን ስለሚናገርና ታረኩም የላም ወተት ለሕፃን ልጅ ቀላል ምግብ እንደሆነ ሁሉ ለአዲሰ አማኝ ቀለል በሎ የቀረበ መሆኑን ያስገነዝባል ።ቅዱስ ሉቃሰ የድንግልና ሕይወት የነበረው ወንጌላዊ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሰማዕትነት እስካረፈበት ጊዜ ድረስ ደቀ መዝሙር በመሆን አገልግሎታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ67 ዓ.ም. በሮማ በሰማዕትነት ሲያርፍ ሉቃስ ወደ ድልማጥያ መጣ በዚያም በሽምግልና ዘመኑ ወንጌልን በመስበክ ላይ እያለ አይሁድና ካህናተ ጣዖት ተባብረው ትምህርቱን በመቃወም ተነሡበት መስከረም 20 ቀን 68 ዓ.ም. አይሁድና አረማውያን ጉባዔ አድርገው ነገር በመሥራት ለሮም ንጉሥ ከሰሱት፡፡ በዚያን ዘመን ኔሮን እብደቱ ያየለበት ጊዜ በመሆኑ የቅዱስ ሉቃስን ከሮሜ ማምለጥና ወደ ድልማጥያ መምጣት ሲሰማ 200 ወታደሮችን ላከበት ቅዱስ ሉቃስም የሰዎችን መምጣት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ያሰተምራቸው የነበሩትን ምእመናን ወደየቤታቸው ላከና በድልማጥያ አጠገብ ወደሚገኘው ባሕር ተጠጋ በባሕሩ አጠገብ አንድ ዓሣ አስጋሪ ቆሟል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ዓሣ አስጋሪው ቀረበና ጨዋታ ጀመሩ ቀስ በቀስም ወንጌል ይሰብክለት ጀመር፡፡ ዓሣ አስጋሪውም ቅዱስ ሉቃሰ የሚነግረውን ሁሉ ሥራውን አቁሞ በደስታ ያዳምጠው ነበር በመጨረሻ እንካ እነዚህ የሕይወትን መገንድ ይመሩሃል አለና የያዛቸውን መጻሕፍት ሁሉ ሰጠው ያም ዓሣ አስጋሪ እጅግ ተደስቶ ዕቃ በሚያስቀምጥበት ቦታ በክብር አኖራቸው ቅዱስ ሉቃስ መጽሐፉን ሰጥቶት ዘወር ሲል የኔሮን ወታደሮች ተረባረቡና ያዙት ከዚያም ወደሮም ተወሰደና የኔሮን ፍርድ ቤት ቀረበ ።ንጉሡ ‹‹በሥራይህ ሕዝቡን የምታስት እስከ መቼ ነው?›› ብሎ ጠየቀው፤ ቅዱስ ሉቃስም ‹‹እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም›› ብሎ መለሰለት፡፡ ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው፤ ‹‹እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይህች እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ በቆረጡትም ጊዜ ‹‹ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ ዕወቅ፤ ነገር ግን የጌታዬና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ፤›ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት፤ ከዚህም በኋላ ለያት፤ በዚያም የነበሩ አደነቁ፤ የሠራዊቱም አለቃና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ፡፡ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ በማዘዙ ቆረጡአቸው፤ የምስክርነት አክሊልም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ያረፈው በ፹፬ ዓመቱ ነው፡፡ከዚህም በኋላ ሥጋውን በማቅ አይበት ውስጥ አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት፤ በአማረ ቦታም አኖሩት፡፡ የወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ አማላጅነት፣ ተረዳኢነትና በረከት አይለየን፤ አሜን! መልአከ ብርሃን ዳንኤል ነቢዩበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ኃላፊ፣ የዳግማዊት ጌቴሴማኒ በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ

“የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ…ወንጌላዊ ።”ቆላስይስ 4፥14 Read More »

“የሚመለከታቸው አካላት የዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሊሠሩ እንደሚገባ በአጽንዖት እናሳስባለን”ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ

ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በደረሰው ጥቃት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ። የብፁዕነታቸው ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ነው። “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዟችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”ዮሐ 16፥33 በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ላይ በደረሰው አሳዛኝ ጥቃት ሕይወታቸውን ባጡ እና በተጎዱ ወገኖቻችን ከልባችን አዝነናል። በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተደጋገመው በዚህ ድርጊት ቤተ ክርስቲያናችንን ከልብ የሚያሳዝን እና የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም ጥያቄ ውስጥ የሚከት በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት የዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሊሰሩ እንደሚገባ በአጽንዖት ለማሳሰብ እንወዳለን።መአቱን በምሕረቱ ቁጣውን በትግዕስቱ ይመልስልን ዘንድ ሁልጊዜም ምላሽ ወደሚሰጠን አምላክ በጸሎት መጠየቅ ይገባናል። የልጆቻችንን ነፍስ ከቅዱሳን ማኅበር እንዲደምርልን፣ ያዘኑ የተከዙ ወገኖቻችንን ከሀዘናቸው እንዲያጽናናልን ጸሎታችን ነው። እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ!አባ ገሪማየጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስየቅዱስ ሲኖዶስ አባል

“የሚመለከታቸው አካላት የዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሊሠሩ እንደሚገባ በአጽንዖት እናሳስባለን”ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ Read More »

“ወኀረዩ እስጢፋኖስሀ ብእሴ ዘምሉእ ሃይማኖተ ወመንፈሰ ቅዱሰ – በእምነትና በመንፈስቅዱስ የተሞላውን እስጢፋኖስን መረጡ” ሐዋ 6፥5

እስጢፋኖስ ማለት አክሊል (ዘውድ)ማለት ነው።በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሀገረ እስራኤል ተወልዷል።አባቱ ስምዖን እናቱ ሐና ይባላሉ። መጀመሪያ ከመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በኋላም ከቅዱሳን ሐዋርያት ተምሯል። የመልካም ዛፍ መልካም ፍሬ ለመሆን የበቃ መንፈሳዊ ወጣት ነበር። ማቴ7፥17 በምእመናን ዘንድ መታመንንና መወደድን ያተረፈ፣ በወጣትነት ጊዜው በመንፈሳዊ ዕውቀትና በመንፈሳዊ ጥበብ ያደገ ፣በሃይማኖት የጸና፣መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ነበር። በአንደኛው መቶ ከፍለ ዘመን ማለትም ከ34-41 ዓ/ም ባለው ጊዜ አይሁድና አሕዛብ ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላ በመካከላቸው መነቃቀፍ ፣መተማማትና አለመግባባት ተፈጥሮ ጉዳዩ ከሐዋርያት ሲደርስ “ኢይደልወነ ከመንኅድግ ቃለ እግዚአብሔር ወንፀመድ ማዕዳተ – የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ አይገባንም” ሐዋ 6፥2 ብለው ችግሩን የሚፈቱ፣ በመልካምነታቸው የታወቁ፣ መንፈስቅዱስ የሞላባቸው፣ ጥበበኞች የሆኑ ሰባት ሰዎች እንዲመረጡ በማዘዛቸው ችግሩን እንዲፈቱ በሕዝቡ ተመርጠው በሐዋርያት ከተሾሙት 7 ዲያቆናት አንዱና ዋናው ነበር። በመሆኑም ሊቀ ዲያቆናት (የዲያቆናት አለቃ) ይባላል። የሐሥ 6፥6 ይሄ ምን ይነግረናል? ሐዋርያት መርጠው እንሹባችሁ አላሉም ።ሕዝቡን ራሳችሁ ምረጡ አሏቸው እንጂ። ይህ ነገርም ሕዝቡን ደስ አሰኝቷል። የአመራረጡ መስፈርት መልካምነት፣ ጸጋ መንፈስ ቅዱስና ጥበብ እንጂ ዝምድና አልነበረም ቀረቤታ አልነበረም ብሔር አልነበረም ቋንቋም አልነበረም እጅ መንሻሞ አልነበረም ጆሮ ጠቢነትም አልነበረም አማላጅም አልነበረም ጮሌነትም አልነበረም። በዚህ ሁሉ የመጣ(የተሾመ)ችግር ከማባባስ ባለፈ ችግር ፈቺ መሆን አይችልም ሰው ያለ ቦታው ተቀምጦ እንዴት ችግር ሊፈታ ይችላል? ለመንፈሳዊ ሹመት መንፈሳዊ ሰው ነው የሚገባው የዛሬዋ ቤተክርስቲያን ከዚህ ምን መማር አለባት ? በሊቀ ዲያቆንነቱ ጊዜ 8000 ማኅበረ ክርስቲያንን መርቷል። በአገልግሎቱ ኦሪት እጠፋ እጠፋ ፣ወንጌል እሰፋ እሰፋ ብላለች። በእኛ የአገልግሎት ጊዜ ክርስቲያንነት እሰፋ እሰፋ፣ ኢክርስቲያንነት እጠፋ እጠፋ ብሎ ይሆን?? በእስጢፋኖስ የአገልግሎት ጊዜ ናዖስ የሚባል መሠርይ (ጠንቅዋይ) (ጠንቋይ) በምትሐታዊ ተአምራት ሕዝቡን ሲያስት እውነተኛ ተአምራትን በማድረግ የናዖስን የምትሐት ሐሰትነትና ከንቱነት ለሕዝብ በማሳየት በእምነቱ እንዲጸና፣በምትሐታዊ ተአምር ከመታለል ራሱን እንዲጠብቅ በማስተማር የዕቅበተ እምነት ተልእኮውን በሚገባ ተወጥቷል። መሠርዩ ናዖስ በምስሐበ አጋንንትወደሰማይ ዐርጋለሁ ሲል በስመ እግዚአብሔር አውርዶ መሬት ላይ የጣለገባሬ ተአምራትም ነው ይባላል።የሐሥ6፥8የሄኖክን የትውልድ ሱባኤ፣የዳንኤልን የሰንበት ሱባኤየኤርምያስን የዕለት ሰባኤ አውጥቶኦሪትን ከወንጌል፣ዘመኑን ከዘመን ፣ትንቢቱን ከመድኅን አስማምቶ ዘመነ ሥጋዌ እንደደረሰ፣እግዚአብሔር ወልድ ሥጋ እንደለበሰ ሲያስተምር”ወሰእኑ ተቃውሞቶ”እንዲል እስጢፋኖስ የሚናገርበትን ጥበብ መቃወም ቢሳናቸው ተበሳጭተው ወደ ዐደባባይ አውጥተው በደንጊያ ወግረው ገድለውታል።እርሱም ሰማዕትነትን ተቀብሏል።ቀዳሜ ሰማዕት ይባላል።የሐዲስ ኪዳን ሰማዕታት መጀመሪያ ማለት ነው።”በእስጢፋኖስ አዕባን እመየኀልቁ፣ወገረኒ ኢያሱ በወርቁ”እንዳለ ባለቅኔው።ኦሪትን በሥርዓተ መላእክት ተቀብያለሁ ብሎ የሚመጻደው፣ነገር ግን ኦሪት የማይጠብቀው የአይሁድ ጉባኤ”ኦሪት ከወንጌል፣ዘመን ከዘመን፣ትንቢቱ ከመድኅን”እንደማይገጥም ለማሳየት ሲሉዓመተ አበውን ለመቀነስ፣ኦሪተ ሌዋውያንን ወደ ኦሪተ አይሁድ ብጡል ለመለወጥ ተገዷል ። “ከሸንጎ ቢረታ ሚስቱን ከቤት መታ” እንደሚባለው ማለት ነው።”እሙንቱሰ እምከንቱ ውስተ ከንቱ”እንዲል አካሔዱም ከጥፋት ወደፋት ሆኖበታል። እስጢፋኖስን እንጂ የእስጢፋኖስን እምነት መግደል አልቻለም “ዛሬም ክርስታያኑን እንጂ ክርስትናን መግደል አይቻልም።ማጥፋት አይቻልም ።መከራ ሊኖር ይችላል።ስደት ሊኖር ይችላል ፣ጫና ሊኖር ይችላል ነገር ግን ክርስቲያንነት ድል ያደርጋል እንጂ ድል አይሆንም።አይሸነፍም። ቅዱስ እስጢፋኖስ ግን “እግዚኦ ስረይ ሎሙ ዘንተ ኀጢአቶሙ ወኢትረሲ ቦሙ ጌጋየ” አቤቱ ይሄን በደል አታድርግባቸው” የሐሥ7፥60 በማለት ከክርስቶስ የተማረውን ይቅር ባይነትን ሉቃ 23፥34 ገዳዮቹን ይቅር በማለትና “ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመጠዋ ለነፍስየ” ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል” የሐሥ 7፥59ከርስቶስን መስሎታል ሉቃ23፥46 1ኛ ቆሮ 11፥1“በዚያን ጊዜም በቤተክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ” የሐሥ 8፥1 ማኅበረ እስጢፋኖስ ወደ እስያ ወቢታንያ ወደ ቀጰዶቅያ ተበትኗል።ይህም ውስጡ ጥበበእግዚአቦሔር ነበር በኢየሩሳሌም በኖሩ ሃይማኖት ይጸናል እንጂ አይሰፋም ነበር አሁን ግን ወንጌልንበደረሱበት ሥፍራ ሁሉ ስለሰብኩ የሃይማኖት መጽናት ብቻ ሳይሆን መስፋትም ሆነ። “እግዚአብሔርን ለሚወዱት እንደ ዐሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን” ሮሜ 8፥28 ጥቅምት 17 ሢመቱ ጥር 1 ዕረፍቱ የሰማዕቱ ረድኤትና በረከት አይለየን። ሊቀ ማእምራን ሰሎሞን ፈጠነ

“ወኀረዩ እስጢፋኖስሀ ብእሴ ዘምሉእ ሃይማኖተ ወመንፈሰ ቅዱሰ – በእምነትና በመንፈስቅዱስ የተሞላውን እስጢፋኖስን መረጡ” ሐዋ 6፥5 Read More »

‎”በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ” (ሐዋ 6:3)‎በዚህ የአባቶቻችን የሐዋርያት መመሪያ መሠረት ከተመረጡ አገልጋዮች መካከል አንዱ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ነው።

በመጋቤ ምሥጢር ጥበቡ አናጋው ‎ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ እግዚአብሔር ልኮት ኢትዮጵያዊውን ጃንረባ ባኮስን ያጠመቀው ነው።‎‎የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታረክ፣ ምስረታ እና ልደት የሚያወሳ የታሪክም ሆነ የቤተክርስቲያን ምሁር ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስን እና ቅዱስ ባኮስን ሳያነሳ ማለፍ አይቻለውም፡፡‎‎ምክንያቱም በኢትዮጵያ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንዲሰበክ መነሻ የሆኑ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የወንጌል አባታቶቻችን ስለሆኑ ነው፡፡‎‎ከሰባቱ ሊቃነ-ዲያቆናት አንዱ ሆኖ የተሾመው ቅዱስ ፊልጶስ ትውልዱ ኢሲዶር ከምትባል የቄሳሪያ የወደብ ከተማ ሲሆን በቅዱስ እስጢፋኖስ ሞት ምክንያት ደቀመዛሙርት ከኢየሩሳሌም እስከተበተኑ ድረስ በኢየሩሳሌም ከሐዋርያት እግር ስር ሆኖ ተምሯል፡፡‎‎ከመንፈስ ቅዱስ መገለጥ በኋላ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ባደረጉት የመጀመሪያ የስብከት አገልግሎት በርካታ ምዕመናን አምነው ተጠመቁ፤ የምዕመናኑ ቁጥር እጅግ በመጨመሩ እና የአገልግሎቱ ዘርፉም እየበዛ በመሄዱ አገልጋዮችን መጨመር አስፈላጊ መሆኑን ባመኑ ጊዜ ሐዋርያት ቀደም ሲል በአርድትነት ሲያገለገሉ ከነበሩት መካከል ሰባቱን ሊቃነ-ዲያቆናት ለመጋቢነት መረጡ፡፡‎‎ምዕመኑን በመጋቢነት እንዲያገለግሉ ከተመረጡት ሰባቱ ሊቀ-ዲያቆናት መካካል አንዱ ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ ዘሰማርያ ወኢትዮጵያ ነው፡፡‎‎በ35ዓ.ም. ቅዱስ እስጢፋኖስ በአይሁድ እጅ በሰማዕትነት ማለፉ ተከትሎ በኢየሩሳሌም የነበሩት ማኅበረ ምዕመናን ተበተኑ፤ ቅዱስ ፊልጶስም ጊቶን ወደ ምትባል የስሞን መሠርይ የትውልድ ስፍራ ወደሆነች የሰማርያ ከተማ ሄደ፡፡‎‎በዚያም ሐዋርያዊ አገልግሎቱን በማጠናከር በርካታ ምዕመናን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምነው እንዲጠመቁ አስችሏል፡፡ በተለይ በጥንቆላ ግብሩ የሚታወቀውን ሲሞን መሠርይን በማሳመን ማጥመቁን ቅዱስ መጽሐፍ ዘግቦለታል፡፡ ሐዋ 8፡13።‎‎በሰማርያ ሳለ የጌታም መልአክ ፊልጶስን ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ አለው፡፡ እርሱም ተነሥቶ ሂደ፡፡ እነሆ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባላሟል እና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘ፡፡‎‎ይህም ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፡፡ ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡ መንፈስም ፊልጶስን “ሂድ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው፡፡ ፊልጶስም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ሂደ፤ ጃንደረባውም የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰምቶ “ለመሆኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው፡፡ ጃንደረባውም “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውለዋለሁ” አለው፤ ቅዱስ ፊልጶስም ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሰበከለት፡፡ በመጓዝ ላይ ሳሉም ውሃ ካለበት ስፍራ ደረሱ ጃንደረባውም “እነሆ ውሃ እዚህ አለ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው፡፡ ፊልጶስም “በፍጹም ልብህ ካመንህ መጠመቅ ትችላለህ” አለው፡፡ ጃንደረባውም ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ›› ሲል መለሰለት፤ ሠረገላውም እንዲቆም አዘዘ፡፡‎‎ከዚያም ሁለቱም አብረው ወደ ውሃው ወረዱ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው፡፡ ከውሃውም በወጡ ጊዜ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጥቆ ወደ አዛጦን ወሰደው። ሐዋ 8፣ 26-39። ወደ ቂሣርያ እስኪመጣ ድረስም በእየከተሞቹ ሁሉ እየተዘዋወረ ወንጌልን ሰብኳል፡፡ በቂሳርያ ሳለ ሚስት አግብቶ 4 ሴቶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው ደናግናል ነበሩ፡፡ ሐዋ 21፣8። በረጅም የወንጌል አገልግሎቱ ብዙ አይሁድን እና ሳምራዊያንን ወደ ክርስትና መልሶ ጥቅምት 14 ቀን በሰላም ማረፉን የታረክ መዛግብት ይናገራሉ፡፡‎‎የሐዋርያው የቅዱስ ፊሊጶስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን! መጋቤ ምሥጢር ጥበቡ አናጋው ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም

‎”በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ” (ሐዋ 6:3)‎በዚህ የአባቶቻችን የሐዋርያት መመሪያ መሠረት ከተመረጡ አገልጋዮች መካከል አንዱ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ነው። Read More »

የሕግ ክፍልን በተመለከተ የግንዛቤ መስጫ መርሃግብር ተካሄደ!!

ኤክቱስ ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የሕግ ክፍል ዐቢይ ኮሚቴ መቋቋሙን ተከትሎ ለተመረጡ ወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች፣ ለአድባራት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ አባላት የግንዛቤና የትውውቅ መርሃግብር የተካሄደ ሲሆን በመርሃግብሩ የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። መርሃግብሩ በዘርፉ ባለሙያዎች ስለአስፈላጊነቱ እና ስለዝርዝር ጉዳዮች ገለጻ የተደረገ ሲሆን ሁሉም የኮሚቴው አባላት ራሳቸውን ለመርሃግብሩ ተሳታፊዎች አስተዋውቀዋል። በተጨማሪም ከተሳታፊዎች ሃሳብ፣ አስተያየት እና ጥያቄ የቀረበ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎች የኮሚቴው አባላት ምላሽ ሰጥተዋል። በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ መንፈሳዊ ትምህርትና የካህናት አገልግሎት ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ምሕረቱ በጸሎት ፈጽመዋል።

የሕግ ክፍልን በተመለከተ የግንዛቤ መስጫ መርሃግብር ተካሄደ!! Read More »

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ በክብር ዶክተር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ እረፍት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ!!

ኤክቱስ ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በቀድሞ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት በነበሩት የክብር ዶክተር በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ከዚህ ዓለም ድካም በማረፋቸው ምክንያት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል። ብፁዕነታቸው በመልእክታቸው እንደሀገረ እንደርሳቸው ያለ አስታራቂ፣ የዋህ እና ደግ አረጋዊ አባት ማጣታችን ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም ለመላው የእስልምና እምነት ተከዮች፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸው መጽናናትን ይላክልን ብለዋል።

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ በክብር ዶክተር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ እረፍት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ!! Read More »

ኢ-አማንያን የሥላሴን ልጅነት እንዲያገኙ እና የንስሐ አባት የሌላቸው ምዕመናን እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ!!

ኤክቱስ ጥቅምት 9/2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በይርጋጨፌ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘው የይርጋጨፌ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አከባቢ ባሉ አዳሜና ኦሩ በተላ አከባቢ የሚኖሩ የንስሐ አባት የሌላቸው እና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጠፍተው የነበሩትን የመፈለግ ሥራ ተጠናክሮ እየተሠራ እንደሚገኝ መስከረም ሃያ ስድስት ቀን በነበረው ዘገባችን መዘገባችን ይታወሳል። በሁለቱ ቀበሌዎች ሁለት የስብከት ኬላዎች የተቋቋአ ሲሆን በዛሬው ዕለት የንስሐ አባት የሌላቸው እንዲኖራቸው በማድረግ በተሠራው ሥራ 8 አዳዲስ አማንያን ሥርዓተ ጥምቀት የተፈጸመላቸው ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ አንዲት እኅት በቄደር ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተመልሳለች። በአጠቃላይ ከዚህ በፊት ከተደረጉት መርሃግብራት ጋር 32 አዳዲስ አማንያን መገኘታቸው ተገልጿል። በተጨማሪም በካህናት እጦት ምክንያት 170 የንስሐ አባት የሌላቸው ምዕመናን እንዲኖራቸው፣ 44 የሰንበት ተማሪ ያልነበሩ ሕጻናትና ወጣቶች በሰንበት ትምህርት ቤት መዋቅር እንዲታቀፉ፣ እንዲሁም አንዲት የመቶ ሃያ ስምንት ዓመት ዕድሜ ያላቸው እናት ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን እንዲቀበሉ የማድረግ ሥራ መሠራቱ ተገልጻል። በመርሃግብሩም የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ፣ የሀገረ ስብከቱ ቁጥጥርና ምግባረ ሰናይ ክፍል ኃላፊ መምህር በየነ ክፍሌ፣ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ይባቤ ይልማ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ኄራን ቀሲስ ጫንያለው፣ ሰባኪያነ ወንጌል፣ ዘማርያን እንዲሁም ካህናትና ምዕመናን ተገኝተዋል። ይህ የተጠናከረ ሥራ በሁሉም አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ መሠራት እንዳለበት ተጠቁሟል። ፎቶ ልጅ ሀፒ

ኢ-አማንያን የሥላሴን ልጅነት እንዲያገኙ እና የንስሐ አባት የሌላቸው ምዕመናን እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ!! Read More »

Scroll to Top