ኤክቱስ ሰኔ 27/2018 ዓ.ም
“ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር ባርክናክሙ እምቤተ እግዚአብሔር – በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው በእግዚአብሔር ስም መረቅናችሁ” መዝ 117፥26
- የሀገረ ስብከታችን ሥራ አስኪያጅና የየክፍል ሠራተኞች
- የየወረዳ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጆችና ጸሐፍት
- የየአድባራቱ አስተዳዳሪዎች
- ባለድርሻ ተጋባዥ እንግዶች
- ተመራቂ ደቀ መዛሙርትና የተመራቂ ቤተሰቦች
- ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች
ውድ የቤተ ክርስቲያን ልጆች
በመጀመርያ በዚህ ታላቅና ታሪካዊ የሁለተኛ ዙር የምረቃ መርሃግብር ላይ አብራችሁን ስላላችሁ በቅድሚያ “እንኳን ደኅና መጣችሁ” ለማለት እንወዳለን።
ዛሬ የምንገኘው ለአሥር ወራት የተሰጣቸውን ትምህርት ሌሊት ከቀን በከፍተኛ ትጋት ሲከታተሉ የቆዩትን ደቀ መዛሙርቶቻችንን የምርቃት በዓል ለማክበር ነው። ውድ ደቀ መዛሙርት ሆይ ለዚህ ታላቅ ማዕረግና ስኬት በመብቃታችሁ “እንኳን ደስ አላችሁ” እያልኩ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን አምላካዊ ተልዕኮ ተቀብላችሁ በጥንካሬና በብቃት እንድትወጡ መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን።
ወድ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
በሀገረ ስብከታችን ከ2016 ዓ.ም በፊት ምንም ዓይነት የተደራጀ የአብነት ትምህርት ቤት ባለመኖሩ በገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን ውዳሴ ማርያም በአግባቡ የተማረ ዲያቆን ማግኘት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ከመቅረፍ አንጻር ሀገረ ስብከታችን የ10 ዓመት ሥልታዊ ዕቅድን ከምንም ተነስቶ በቁርጠኝነት አሳካዋለሁ ብሎ ያስቀመጠውን ግብ ወደ ተግባራዊ ዕቅድ በመቀየር አንድ ብሎ በ2017 ዓ.ም ጉዞውን በስድስት ደቀ መዛሙርት መቃብር ቤቶችን በማደስ፣ ቀለባቸውን፣ መኝታቸውንና ሕክምናቸውን ጨምሮ ሙሉ ወጫቸውን በመሸፈን ጀመረ።
ይህ በቅንነት የተዘራአ ዘር አድጎና ጎምርቶ በ2018 ዓ.ም አቅሙን በማሳደግ 17 ደቀ መዛሙርትን ተቀብሎ ማስተማር ችሏል። ዛሬ የምናስመርቃቸው ከእነዚህ ውስት 14ቱን ሲሆን ሦስቱ የሐዲሳት ደቀ መዛሙርት በመሆናቸው ለቀጣዩ ሦስት ዓመታት ከትምህርት ቤቱ ጋር የሚዘልቁ ናቸው። የዚህ የአብነት ትምህርት ቤት ጉዞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳየው ዕድገት የእግዚአብሔር ቸርነት ታክሎበት የእናንተ ልግስና ውጤት በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ።
ይህ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሳካ በተለይም የደቀ መዛሙርቱን የቀለብና የዕለተዕለት ፍላጎት በመደፍ መንፈሳዊ ግዴታችሁን የተወጣችሁ ማኅበረ ቅዱሳን ዋና ማእከል፣ ማኅበረ አቡቀለምሲስ እና ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ ከኢትዮጵያ… መልአከ ሣህል ቀሲስ አወቀ፣ ቤተልሔምና ቤተሰቦቿ፣ እኅታችን ሃና ከአሜሪካ እንዲሁም የሀገረ ስብከታችን መማክርት ጉባኤ የእናንተ እጅ መዘርጋት ዛሬ ስለምናየው ፍሬ መሠረት ሆኗልና በእግዚአብሔር ስም የላቀና የከበረ ምሥጋናዬን በሀገረ ስብከታችን ስም አቀርባለሁ።
በመቀጠልም ጉዟችን በዚህ ብቻ የሚያበቃ ባለመሆኑ ለ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቱን አቅም ይበልጥ በማሳደግ በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ለ32 ደቀ መዛሙርት የሚሆን ዶርሚተሪ፣ መመገቢያ አዳራሽና ማብሰያ፣ የሁለት መምህራን መኖርያ ቤት፣ እንዲሁም ለሁሉም የሚያገለግል የሻወርና የሽንት ቤት ግንባታ ተጀምሮ ሥራው በመፋጠን ላይ ይገኛል። በመሆኑም በቀጣይ የትምህርይ ዘመን አዳዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል በከፍተኛ ዝግጅት ላይ እንገኛለን።
ይህ ትልቅ ራዕይና የጀመርነው የልማት ሥራ ዳር እንዲደርስ እንዲሁም ወደፊት ብዙ ደቀመዛሙርትን አፍርተን ለቤተ ክርስቲያን ለሀገር እንድናበረክት ውድ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ደጋፊዎቻችን ከጎናችን እንዳትለዩ የወደፊት እርዳታችሁንና ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ እያሳሰብኩ ለአንድ ደቀ መዝሙር አንድ ሰው በሚል መሪ ቃል ምእመናንን የዚህ በረከት ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ለማድረግ የጀመርነውን ተግባር ለሌሎች እንዲዳረስ ታደርጉ ዘንድ በታላቅ ትህትና እናሳስባለን።
በመጨረሻም የሁለተኛ ዙር የአብነት ትምህርት ቤት የምረቃ መርሃግብር በይፋ መጀመሩን እያበሰርን መልካም የደስታና የበረከት ጊዜ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።
እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ!
አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና
የቅዱስ ሲኖዶስ አባል
