በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት የዶሮ ልማት ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ!

ኤክቱስ ሰኔ 6/2018 ዓ.ም

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ቀደም ሲል በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እና በአንዲዳ የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ የተደረጉትን ተሞክሮዎች መሠረት በማድረግ በዛሬው ዕለት በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ ፕሮጀክቱን ለመጀመር የሥጋ ዶሮዎች ጫጩቶችን ግዢ ፈጽሟል። ይህ እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያን ከመንፈሳዊ አገልግሎቷ ጎን ለጎን ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት የሚያጠናክር ነው።

ይህንኑ የልማት ሥራ በጥራትና በስኬት ለመምራት እንዲቻል ሀገረ ስብከቱ ላለፉት ዕለታት ለዶሮዎቹ መኖሪያ የሚሆኑ ዘመናዊ ቤቶችን በጥናት ላይ በተመሠረተ መልኩ በሥራ ላይ ሲገነባ ያሳለፈ ሲሆን ይህ ቅድመ-ዝግጅት የዶሮዎቹን ደህንነት ለመጠበቅና ምርታማነታቸውን አስተማማኝ ለማድረግ ታስቦ የተከናወነ ተግባር መሆኑ ተገልጿል።

ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበትም ሀገረ ስብከቱ ለተዘጋጀው ዘመናዊ መጠለያ የሚሆኑ ዘጠኝ መቶ አምስት (905) ዶሮዎችን ግዢ አከናውኗል።

የዚህ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ አድባራት ሁሉ የሀገረ ስብከቱን አርአያነት፣ አሠራርና የጥናት ተሞክሮ ዋቢ በማድረግ በየአካባቢያቸው በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ማነቃቃትና ማበረታታት እንዲሁም ከሙዳየ ምጽዋት በመላቀቅ በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

Scroll to Top