በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ብፁዕ አቡነ ገሪማ የ2018 ዓ.ም ጾመ ሐዋርያትን በማስመልከት ያስተላለፉት መልእክት!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት፣ በሀገር ውስጥና በተለያዩ ክፍላተ ዓለም የምትኖሩ ውድ የቤተክርስቲያናችን ልጆች ምእመናንና ምእመናት፤ በመጀመሪያ ለቅዱሳን ሐዋርያት ጾም በሰላም አደረሳችሁ።

«ወእምዝ ጾሙ ወጸለዩ ወወደዩ እደዊሆሙ ዲቤሆሙ ወፈነዎሙ — ከዚህ በኋላ ጾሙ፣ ጸለዩም፣ እጃቸውንም ጫኑባቸው፣ ሰደዷቸውም» (የሐዋ. ሥራ 13፥3)

ይህ የሐዋርያት ጾም ቤተክርስቲያን ከምትጾማቸው ሰባቱ አዋጅ ጾሞች መካከል አንዱ ነው። ሐዋርያት ይህንን ጾም የጾሙት ከራሱ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አርአያነት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል፣ ሳያድርና ሕዝባዊ አገልግሎቱን ሳይጀምር ወዲያውኑ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሄድ ፵ መዓልትና ፵ ሌሊት መጾሙን ቅዱስ ወንጌል ይመሰክራል። ጌታችን የጾመው እርሱ ጾም አስፈልጎት ሳይሆን ለእኛ የሕይወትን መንገድ ሊያሳየንና ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎትና ድል የሚገኘው በጾም መሆኑን ሊያስተምረን ነው።

ቅዱሳን ሐዋርያትም የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናቸው ከመምህራቸው የተማሩትና የተረዱት ይህንን ታላቅ ምስጢር ነበር። በጰንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ ጊዜ ወዲያውኑ ወደ ዓለም ስብከት አልተጣደፉም። ይልቁኑ ልክ እንደ ጌታቸው የዓለምን የወንጌል ተልዕኮ ከመጀመራቸውና አገልጋዮችን ለሥራ ከመሰማራታቸው በፊት ጾምንና ጸሎትን አስቀደሙ። በርእሳችን ላይ እንደጠቀስነው ወንጌልን ለአሕዛብ ለማድረስ በርናባስንና ሳውልን ለሥራ ከመለየታቸውና እጃቸውን ጭነው ከመስደዳቸው በፊት መሠረታቸውን ያጸኑት በዚህ በጾምና በጸሎት መንፈሳዊ ኃይል ነበር።

ጾም ማለት ሰማያዊውን ኃይል የምንለብስበት፣ ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍስ የምናስገዛበትና ሰይጣናዊ ፈተናዎችን የምናሸንፍበት መሣሪያችን ነው። ሐዋርያት በጥንቷ ቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ሲሾሙ ፈተናዎችን ሲጋፈጡና አዳዲስ መንፈሳዊ ጉዞዎችን ሲጀምሩ ይዞሙ እንደነበር እኛም ዛሬ በማንኛውም የሕይወት ጎዳናችን ውስጥ ስንጓዝ አስቀድመን በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ እንዳለብን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።

ውድ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤ ዛሬ ሀገራችንም ሆነች ቤተክርስቲያናችን የምትገኝበትን ፈታኝ ወቅት ስንመለከት ይህ የሐዋርያት ጾም ለእኛ ትልቅ የመንፈስ መታደሻ ነው። ሐዋርያት በዘመናቸው የነበረውን ልዩነት፣ መከፋፈልና ጥላቻ በወንጌል ፍቅር ያሸነፉት በጾም በተገኘ ኃይል ነው። እኛም በዚህ ወቅት ከምግብ ከመከልከል ባለፈ ልባችንን ከጥላቻ፣ አንደበታችንን ከክፉ ነገር፣ እግራችንንም ከጥፋት መንገድ ልንጠብቅ ይገባል። እርስ በእርስ መዋደድንና ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ምግባርን በተግባር ልናሳይ ይገባል።

ውድ ምዕመናን ከጥንት ጀምሮ የነበረንን የወንድማማችነትና የፍቅር እሴት ይበልጥ እንድታጠናክር፣ በጾምና በጸሎት ሆነን ለሀገራችን ሰላም እንድንለምን አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

የአባቶቻችን የቅዱሳን ሐዋርያት አምላክ ጾሙን የበረከት፣ የሰላምና የፍቅር ያድርግልን። የቅዱሳን ሐዋርያት አማላጅነታቸውና ጸሎታቸው ከሁላችን ጋር ይሁን!

እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ!

አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

Scroll to Top