በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የመጡ ልዑካን በብፁዕነታቸው መሪነት የመስክ ጉብኝት አደረጉ!

ኤክቱስ የካቲት 4/2018 ዓ.ም

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመጡ ልዑካን በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መሪነት በሀገረ ስብከቱ የሠሩ በርካታ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

በመጀመርያ በአንዲዳ የሚገኘው የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ሂደት፣ የዶሮና የንብ ፕሮጀክቶች፣ የደቀ መዛሙርትና የመምህራን የማደርያ የመመገቢያ እና የመማርያ ክፍሎች እንዲሁም ጽሕፈት ቤት ከተጎበኘ በኋላ የዲላ ዳማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው የንብ ማነብ ሥራ እንዲሁም የእንሰትና የቡና ልማቶች ተጎብኝተዋል።

በመቀጠል ሀገረ ስብከቱ የሚያስገነባው መንበረ ጵጵስና አሁናዊ ሁኔታ፣ የዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው የውኃና የዶሮ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ትምህርት ቤት ተጎብኝቷል።

እንዲሁም በዲላ ዳግማዊት ጌቴሴማኒ በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አዲሱ ጽሕፈት ቤት፣ የደብሩ ትምህርት ቤት እና ሀገረ ስብከቱ አዲስ ፕሮጀክት ለመሥራት ከደብሩ የወሰደው ቦታዎች ከተጎበኙ በኋላ የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ተጎብኝቷል።

መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የጥናትና ምርምር መምሪያ ኃላፊ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የኮሚኒኬሽን ኃላፊ በበኩላቸው ሀገረ ስብከቱ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለመፈጸም እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት አድንቀው ይህንን አገልግሎት ለመደገፍ ከሀገረ ስብከቱ ጎን እንደሚቆሙ ቃል ገብተዋል።

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ልዑካኑ ከሥልጠናው ጀምሮ የነበራቸውን ቆይታ አንስተው እንዲሁም የሀገረ ስብከቱን ሥራዎች ዞረው ስለጎበኙ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Scroll to Top