ኤክቱስ ጥር 4/2018 ዓ.ም
በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ስር በሚገኘው የዲላ ማረሚያ ተቋም የፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሱ ዓመታዊ የፍልሰቱ መታሰቢያ በዓል ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት ተከብሮ ውሏል።
በዲላ ከተማ የሚገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በሥፍራው ተገኝተው የዕለቱን በዓል የሚገልጽ ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል።
ይህ በማረሚያ ተቋሙ ውስጥ የሚገኘው የፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ለታራሚዎች መንፈሳዊ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ በሥነ-ልቦና ጥንካሬ እና በሥነ-ምግባር ታንጸው እንዲወጡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ የሀገረ ስብከቱ የምግባረ ሰናይ ክፍል ኃላፊ መምህር በየነ ክፍሌ ገልጸዋል።
በዕለቱ ብፁዕነታቸው ለታራሚዎች እና ለበዓሉ ታዳሚዎች የዕለቱን ትምህርት አስተምረዋል።
ብፁዕነታቸው በትምህርታቸው የቅዱስ ዮሐንስን የፍቅርና የጽናት ሕይወት መነሻ በማድረግ፣ ታራሚዎች በማረሚያ ቆይታቸው በሥነ-ምግባር ታንጸው ለተሻለ ሕይወት እንዲዘጋጁ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም የሕግ ታራሚዎቹ በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚያሳልፉት ጥቂት ጊዜ ብቻ መሆኑን በመግለጽ ከዚህ በላይ ግን ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ከዘለዓለም እስራት ነጻ መውጣት እንደሚገባ በመግለጽ መርሃ-ግብሩን በጸሎት አጠናቅቀዋል።
