በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

እመኬ ፈቀድኩ የሀሉ እስከ ሶበ እመጽእ ሚ ላዕሌከ(እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ?) ዮሐ ፳፩ ፥ ፳፪

ጥር ፬ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ከዚህ ዓለም የተሰወረበት ዕለት ነው ።
የቅዱስ ዮሐንስን መሰወር ከመናገራችን በፊት ቅዱስ  ዮሐንስ ወንጌላዊ ማን ነው ?ምን ምን አደረገ የሚሉትን ነጥቦች በአጭር እንመልክት።
ቤተሰቦቹ፦ የቅዱስ ዮሐንስ አባቱ ዘብዴዎስ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ማቴ 4፥21 እናቱንም የዘብዴዎስ ልጆች እናት በማለት ስሟን ሳይጠራ ይገልጣታል። ማቴ 27፥56 20፥22 የትርጓሜ ሊቃውንት ግን ማርያም ባውፍልያ ናት በማለት ገለጠዋታል።
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንሰ ክርስቶስን ከመከተሉ በፌት    የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ነበር። ዮሐንስ መጥምቅ እነሆ የእግዚአብሔር  በግ ብሎ ሲያስተምር ሰምተው ክርስቶስን ከተከተሉት ከሁለቱ ደቀመዛሙርት ስሙ ያልተጠቀሰው  አንዱ ዮሐንስ ወንጌላዊ ነው ዮሐ 1፥35-41።

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ለሐዋርያነት የተጠራው ከአባቱና ከወንድሙ ጋር በገሊላ ባሕር ዓሣ ሲያጠምድ ነው ።እነርሱም ከወንድሙ ጋር ዓሣ የሚያጠምዱበትን መረብ እና አባታቸውን በመተው ክርስቶስን እንደተከተሉት በመጽሐፍ ቅድስ ተመዝገቧል ማቴ 4፥21 ክርስቶስን ለመከተል ዓለማዊ ነገርን ሁሉ ትቶ መከተል እንደሚገባ የተማርነው ከሐዋርያት ነው ። ክርስቶስን ለመከተል መረብን(ወጥመድን) መተው ያስፈልጋል።አንድ አንድ ጊዜ ዓሣ የምናሠግርበት መረብ እኛን የሚያሠግርበት አጋጣሚ ይፈጠራል ስለዚህ  መረብን መተው ክርስቶስን ለመከተል ቁልፍ ጉዳይ ነው ። መረብ ለዓሣ አሥጋሪ የኑሮ መሠረትና  ሀብት ነው ። ዮሐንስ ግን ዘለዓለማዊውን ሀብት ክርስቶስን ለማግኘት ጊዜያዊውን ሀብት መረቡን ትቷል።

የዮሐንስ ስሞች፦ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን ከተከተለ በኋላ ብዙ ስሞች ተሰጥተውታል እነርሱም ፦
              1 ወልደ ነጎድጓድ ተብሏል
              2 ፍቁረ እግዚእ   ተብሏል
              3 ቴዎጎሎስ/ታዎጎሎስ ተብሏል
              4 አቡቀለምሲስ ተብሏል
1ኛ ወልደ ነጎድጓድ ብሎ የሰየመው መድኅነ ዓለም ክርስትስ ነው ። ዮሐንስንና ወንድሙ ያዕቆብን በአኔርጌስ ብሏቸዋል ትርጉሙም  ደቂቀ ነጎድጓድ/የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው ማር 3፥17ይህም  ማለት ደቂቀ ምስጢር ማለት ነው። ይህም ስም ለቅዱስ  ዮሐንስ ይስማማዋል ብዙ ምስጢራት በራዕይ ተገልጠውለታልና።
2ኛ ፍቁረ እግዚእ (ጌታ የሚወደው ደቀመዛሙር )  ተብሏል ይህ
ስያሜ በዮሐ 13፥23 ላይ ተመዝግቧል ። ጌታ የሚወደው መባሉም ከሌሎች ደቀ መዛሙርቱ አብልጦ ይወደው ስለነበረ ነው። ከሌሎች በተለየ የዮሐንስ መወደዱ ዮሐንስ በእምነቱ ጠንካራ ስለነበረ ነው።ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ከመስቀሉ ሥር የተገኘ ዮሐንስ ብቻ ነውና ዮሐ19፥26 በዚህም  በእምነቱ ምን ያህል  ጠንካራ እንደሆነ እንረዳለን።
  3 ቴዎሎጎስ /ታዎሎጎስ ተብሏል። ነባቤ መለኮት ማለት ነው  ይህም ማለት የአምላክን የመለኮትን ነገር የተናገረ ማለት ነው ። ዮሐንስ ነባቤ መለኮት የተባለበት ምክንያት «በመጀመርያ ቃል ነበረ » ዮሐ1፥1በማለት የወልድን መለኮታዊ ህልውና፣የወልድን ቀዳማዊነት እና የዓለማት ሁሉ ፈጣሪ መሆኑን ስለ ተናገረ ነው።
4 አቡቀለምሲስ ይባላል ።አቡቀለምሲስ የጽርዕ ቃል ነው። በግእዝ አበ ራዕይ አበ ትንቢት ማለት ሲሆን በአማርኛ ደግሞ ባለ ትንቢት የትንቢት ባለቤት ባለ ራዕይ የራዕይ ባለቤት ማለት ነው ።ሁለተኛው ትርጉም ረዐየ ኅቡአት/የተሰወሩ ነገሮችን የሚያይ ማለት ነው ።

ዮሐንስ በልዩ ልዩ ፀጋዎች የደመቀ ሐዋርያ ነው ።ፀጋውም፦ ንጽሕና ፣ ቅድስና እና ድንግልና ናቸው።እንደ ዮሐንስ ስለ ንጽሕና የተነገረለት ሐዋርያ የለም።ቅዱስ ያሬድ ዮሐንስን ስለ ንጽሕናው እንዲህ  ይገልጠዋል፦ ለትጉሓን ይኤምሮሙ እስመ ኀብረ ንጽሐ ምሥሌሆሙ ዮሐንስ ክቡር ሰባኬ ወንጌል መምህር ወድንግል /ወንጌልን የሚሰብክ ክቡር መምህር ዮሐንስን መላእክትን ይመለከታቸዋል ፤ በንጽሕና ከእነርሱ ጋር አንድ ሆኗልና በማለት የዮሐንስን  ንጽህና ይገልጠዋል።/ድጓ ገጽ 191/
ሀገረ ስብከቱ፦ ሐዋርያት ጌታ ካረገ በኋላ መንፈስ ቅዱስንም ከተቀበሉ በኋላ ይህን  ዓለም  በዕጣ ተካፍለው ለስብከተ ወንጌል ወጥተዋል።ዕጣ በሚጣጣሉበትም ጊዜ ምድረ ጽርዕ /ግሪክ/ለቅዱስ ዮሐንስ ደርሳዋለች። በምድረ ጽርዕ በኤፌሶን አርጤምስ የምትባል ጣዖት ትመለክ ነበር። ዮሐንስ ሰው በሚመለከት ሀገር አልሄድም ብሎ ነበርና ቅዱስ ጴጥሮስ አጽናንቶ ወስዶ አድርሶት ተመልሷል።እንዲህ ሆኖ ቢሄድም ቅሉ ወንጌልን ለማስተማር ምቹ ሁኔታ ባለማግኘቱ ምክንያት ከደቀ መዝሙሩ ከአብሮኮሮስ ጋር በመመካከር ከአንዲት ሮምና ከምትባል ሴት ቤት አግልጋይ በመሆን ገቡ።ዮሐንስ ለውሽባ ቤት እሳት  አንዳጅ ሆነ።ደቀመዝሙሩ አብሮኮሮስም አጣቢ/ጽዳተኛ/ሆነ።ሮምናን በተአምራት /የሞተውን  ልጅ በማስነሳት/አሳምነው አግልግሎታቸውን ጀምረዋል።
በጣም የሚገርመኝ ግን ፦ አባቶቻችን ሐዋርያት የክርስቶስን ወንጌል ለዓለም ለማዳረስ ብዙ ዓይነት መንገዶችን ተጠቅመዋል  የጽዳት ሰራተኛ በመሆን ፣ከሕመምተኞች ጋር ሕመምተኛ  በመሆን ፣የውሽባ ቤት እሳት አንዳጅ በመሆን…አስተምረዋል። የእኛ ዘመን ሐዋርያት ግን ይገርሙኛል ለ3 ቅን አገልግሎት 50እና 60 ሺህ ብር ይጠይቃሉ የሚገርም ነው! ይህም እንኳ ተከፍሏቸው  በሰዓት  ቢገኙ መልካም ነበር። ምን አልባት እነ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ የሰባኪዎችን ሁኔታ በአካለ ስጋ ቢያዩት ምን ይሉ ይሆን! ቅዱስ ዮሐንስ ግን የክርስቶስን ወንጌል ያስተማረ የቤት ሰራተኛ በመሆን ነበር። ያውም የሞተውን  ልጅ አስነስቶ  ቅድስናው እስኪታወቅ ድረስ በመገፋትና በመለጋት ነበር። ይህን ድንቅ ተአምር ከፈጸመ  በኋላ ግን ሮምናን ከነቤተሰቦቿ  የክርስቶስን  ልጅነት እንድታገኝ አስተምሯታል።

በኋላም ከንጉሡ ጀምሮ እስከ ሕዝቡ ድረስ በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል።ቅዱስ ዮሐንስም ወንጌልን እያስተማረ ብዙ ድንቅ
ድንቅ ተአምራትን አያደረገ ብዙ ዘመን  ኑሯል ። ለሕዝቡም               ካህናትን ዲያቆናትን ከሾመላቸው በኋላ  ወደሌሎች አቅራቢያ ሀገሮች ሄደ።በመጨረሻም በከሀዲውና በጨካኙ ንጉሥ በድምጥያኖስ ዘመን በጣዖት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ ። በፈላ ውኃ ካሠቃዩት በኋላ በፍጥሞ ደሴት አጋዙት ።በዚያም ሳለ ራዕዩን አይቶ ጻፈው ።ክፉዎች  ያሰቃየነው ቢመስላቸውም እግዚአብሔር ግን ለራዕይ ተስማሚ የሆነ ቦታ አዘጋጅቶለት ነበር!
ድምጥያኖስ ከሞተ በኋላ ከግዞት ተመልሶ ወንጌሉንና ሶስቱን መልእክታቱን ጽፋል።እግዚአብሔር ሙት ያላለውን መግደል ስለማይቻል ከሳሾቹ ሲሞቱ እንዲሞት የተፈረደበት ቅዱስ ዮሐንስ ግን በሕይወት ወደቦታው ተመልሶ ወንጌልን ያህል  የአምላኩን ቃል ለመጻፍ በቃ።እግዚአብሔር ሲመርጥ ከግዞት ቤት አውጥቶ ሥራ  ያሠራል /ወንጌልን ያጽፋል/። አንዳዱ ደግሞ ከክርስቶስ ወንጌል ወጥቶ  በሉተር ተረት ያብዳል።ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ከማስተማር በተጨማሪ ታዋቂ እና የተዋጣለት ስዕል ሳይ ነበር።
የክርስቶስን ስዕለ ስቅለት በመጀመርያ የሳለው እርሱ ነው ።ቅዱስ ዮሐንስ ከሶስቱ  የምስጢር ደቀመዛሙርት አንዱ ነው እናታችን ድንግል ማርያምንም ከመስቀሉ ስር በእናትነት የአዳምን ልጆች ወክሎ የተቀበለ እርሱ ነው ። እንዴት ያስደስታል የሚወዳትን  እናቱን ለሚወደው ደቀመዝሙሩ  ሰጠው ።ለድንግሉ ደቀመዝሙሩ ድንግል እናት ሰጠው።ቅዱስ ዮሐንስ እስከ መጨረሻው መጽናቱ ድንግል ማርያምን በእናትነት ለመቀበል አብቅቶታል ።ዮሐ 19፥26 ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ሁሉም ሐዋርያት ሲበተኑ እርሱ ብቻ ቅርቶ ነበርና ነው ።

በመጨረሻም ከዚህ ዓለም የሚሰወርበት ጊዜ ሲደርስ 99 ዓም ደቀመዛሙርቱን የመቃብር ገደል አስቆፍሮ ለኤፌሶን ሰዎች በተማራችሁበት ትምህርት  ጸንታችሁ ኑሩ የሚል መልእክት አስተላልፎላቸው ከዚያ ውስጥ ገብቶ ከጸለየ በኋላ እንደ ሄኖክና እንደ ኤልያስ ወደ ብሔረ ሕያዋን ሄዷል።ከላይ በርእሱ እንደተጠቀሰው  አስቀድሞ ጌታ የሐንስ እስከ ዳግም ምጽአት ሞትን እንደማይቀምስ ተናግሮለት ስለ ነበር ሞትን አልቀመሰም። ዮሐንስ ሞትን እንደ ማይቀምስ ሁለት ጊዜ ተናግሯል፦
   1እውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ በመንግሥቱ እስኪመጣ ሞትን የማይቀምሱ አሉ ብሎ ነበር ሜቴ16፥28 በዚህ  ንባብ ውስጥ ማን እንደ ማይሞት አልተጠቀሰም ነገር ግን የሞይሞት እንዳለ ተገልጧል።
   2 ሁለተኛው እኔ እስክመጣ ቢኖር ምን  አግድህ?ያለው ነው ዮሐ 21፥22 በዚህ ንባብ ውስጥ ደግሞ ዮሐንስ ሞትን እንደማይቀምስ በግልጥ ክርስቶስ አስተሞሯል። ስለዚህ ቅዱስ ዮሐንስ  ወንጌላዊ ሞትን አልቀመሰም።ጥር አራት ቀን ወደ ብሔረ  ሕያዋን ሄዷል።

Scroll to Top