በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል በጪጩ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ገሪማ በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ድምቀት ተከበረ!

ኤክቱስ ታኅሣሥ 19/2018 ዓ.ም

ሁልጊዜም ታኅሣሥ አስራ ዘጠኝ ቀን የሚከበረው የታላቁ መልአክ የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በጪጩ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲይና የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ገሪማ በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

ታቦቱ ከመንበሩ ከመውጣቱ በፊት መምህር እስራኤል ብርሃኑ በጌዴኡፋ ቋንቋ ለዕለቱ የሚሆን ትምህርት አስተምረዋል።

ታቦቱ ከመንበሩ ከወጣ በኋላ በደብሩ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ወረብ ቀርቦ የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ማዘንጊያ ኢያቶ ንግግር አድርገዋል።

በመቀጠል በመጋቤ ሐዲስ ዮሐንስ ማሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ ሰባኬ ወንጌልና የታላቁ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር ምክትል ዲን የዕለቱ ትምህርት ተሰጥቷል።

ስእለት፣ መባ እና ሥጦታ የመቀበል መርሃግብር በመምህር ስንታየሁ እና በሊቀ ትጉሃን ሀብታሙ አበበ ተከናውኗል።

በመጨረሻም በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ ጋባዥነት ብፁዕነታቸው ለሕዝቡ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በመስጠት በጸሎት ፈጽምዋል።

Scroll to Top