በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

“የሚመለከታቸው አካላት የዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሊሠሩ እንደሚገባ በአጽንዖት እናሳስባለን”ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ

ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በደረሰው ጥቃት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ።

የብፁዕነታቸው ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ነው።

“በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዟችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”
ዮሐ 16፥33

በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ላይ በደረሰው አሳዛኝ ጥቃት ሕይወታቸውን ባጡ እና በተጎዱ ወገኖቻችን ከልባችን አዝነናል። በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተደጋገመው በዚህ ድርጊት ቤተ ክርስቲያናችንን ከልብ የሚያሳዝን እና የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም ጥያቄ ውስጥ የሚከት በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት የዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሊሰሩ እንደሚገባ በአጽንዖት ለማሳሰብ እንወዳለን።
መአቱን በምሕረቱ ቁጣውን በትግዕስቱ ይመልስልን ዘንድ ሁልጊዜም ምላሽ ወደሚሰጠን አምላክ በጸሎት መጠየቅ ይገባናል።

የልጆቻችንን ነፍስ ከቅዱሳን ማኅበር እንዲደምርልን፣ ያዘኑ የተከዙ ወገኖቻችንን ከሀዘናቸው እንዲያጽናናልን ጸሎታችን ነው።

እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ!
አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስ
የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

Scroll to Top