በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ኢ-አማንያን የሥላሴን ልጅነት እንዲያገኙ እና የንስሐ አባት የሌላቸው ምዕመናን እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ!!

ኤክቱስ ጥቅምት 9/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በይርጋጨፌ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘው የይርጋጨፌ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አከባቢ ባሉ አዳሜና ኦሩ በተላ አከባቢ የሚኖሩ የንስሐ አባት የሌላቸው እና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጠፍተው የነበሩትን የመፈለግ ሥራ ተጠናክሮ እየተሠራ እንደሚገኝ መስከረም ሃያ ስድስት ቀን በነበረው ዘገባችን መዘገባችን ይታወሳል።

በሁለቱ ቀበሌዎች ሁለት የስብከት ኬላዎች የተቋቋአ ሲሆን በዛሬው ዕለት የንስሐ አባት የሌላቸው እንዲኖራቸው በማድረግ በተሠራው ሥራ 8 አዳዲስ አማንያን ሥርዓተ ጥምቀት የተፈጸመላቸው ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ አንዲት እኅት በቄደር ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተመልሳለች። በአጠቃላይ ከዚህ በፊት ከተደረጉት መርሃግብራት ጋር 32 አዳዲስ አማንያን መገኘታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም በካህናት እጦት ምክንያት 170 የንስሐ አባት የሌላቸው ምዕመናን እንዲኖራቸው፣ 44 የሰንበት ተማሪ ያልነበሩ ሕጻናትና ወጣቶች በሰንበት ትምህርት ቤት መዋቅር እንዲታቀፉ፣ እንዲሁም አንዲት የመቶ ሃያ ስምንት ዓመት ዕድሜ ያላቸው እናት ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን እንዲቀበሉ የማድረግ ሥራ መሠራቱ ተገልጻል።

በመርሃግብሩም የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ፣ የሀገረ ስብከቱ ቁጥጥርና ምግባረ ሰናይ ክፍል ኃላፊ መምህር በየነ ክፍሌ፣ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ይባቤ ይልማ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ኄራን ቀሲስ ጫንያለው፣ ሰባኪያነ ወንጌል፣ ዘማርያን እንዲሁም ካህናትና ምዕመናን ተገኝተዋል።

ይህ የተጠናከረ ሥራ በሁሉም አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ መሠራት እንዳለበት ተጠቁሟል።

ፎቶ ልጅ ሀፒ

Scroll to Top