ኤክቱስ ጥቅምት 5/2018 ዓ.ም
ከተጀመረ ሁለተኛ ቀኑን በያዘው ፵፬ተኛው ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በ2017 በጀት ዓመት ያሳካውን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ሪፖርት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ አቅርበዋል።
በሪፖርቱ እንደተገለጸው ሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የቤተ ክርስቲያንን ልጆች በማስተባበር የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን እንዳስከፈቱ የተገለጸ ሲሆን በሁሉም ወረዳ ቤተ ክርስቲነት በመዘዋወር ሀዋርያዊ አገልግሎታቸውን መፈጸማቸውም ተገልጿል።
የአብነት ትምህርት ቤትን በተመለከተ በአንዲዳ ለመጀመርያ ዙር የአብነት ተማሪዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በሟሟላት እና የቅዳሴ መምህር በመቅጠር ትምህርት እንዲሰጥ እንደተደረገ ተገልጿል።
በተጨማሪም በሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ከ20 በላይ በተመረጡ አብያተ ክርስቲያናት ሕዝባዊ መንፈሳዊ ጉባኤያት የተደረገ ሲሆን በስድስቱም ወረዳ ቤተ ክህነቶች ካለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ 3372 አዳዲስ አማንያን መጠመቃቸውን ገልጸዋል።
