“ለእመ አሐዱ አባል ሐመ የሐምም ምስሌሁ ኩሉ ነፍስትነ ወእመኒ ተፈሥሐ አሐዱ አባል ይትፌሣሕ ምስሌሁ ኩሉ ነፍስትነ – አንድ ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ አንድ ብልትም ቢከብር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል”
፩ኛ ቆሮ ፲፪፥፳፮
በቅርቡ በአርሲ ሀገረ ስብከት በሚገኙ በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት በሰው ሕይወት እና በአካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል። በዚህ አስከፊ ድርጊት የተጎዱ እና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋም እና አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ቤተክርስቲያናችን የበኩሏን ኃላፊነት እየተወጣች ትገኛለች።
ይህንን አስመልክቶ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፤ በዚሁ መሠረት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ባስተላለፉት አባታዊ መመሪያ በሀገረ ስብከቱ ሥር በሚገኙ በሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን ጀምሯል። ይህ ኮሚቴ ከምዕመናን የሚሰበሰበውን ድጋፍ ግልጽ በሆነ መንገድ ለተጎጂ ወገኖቻችን እንዲደርስ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ስለሆነም «አንድ ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ» (1ኛ ቆሮ. 12፡26) እንዲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መላው በሀገረ ስብከታችን የምትገኙ ዉሉደ ክህነት እና ምዕመናን በችግር ላይ ለሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያለንን ክርስቲያናዊ ፍቅርና አጋርነት የምናሳይበት ወቅት በመሆኑ፤ የተቻላችሁን ሁሉ ድጋፍ እንድታደርጉ ሀገረ ስብከቱ ጥሪውን ያስተላልፋል።
የባንክ አካውንት ቁጥር: -3491112959532019
የባንክ ስም:- ዓባይ ባንክ
የሂሳብ ስም:- GEDEO KORE AND BURJI HAGERE SIBKET MIGBARE SENAY
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከትሕዝብ ግንኙነት ክፍል
ኤክቱስ ኅዳር 4/2019 ዓ.ም.
