በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት!

ኤክቱስ ጥር 10/2018 ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

በሀገረ ስብከታችን፣ በሀገር ውስጥና በሌሎች ክፍላተ ዓለም የምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናን ወምእመናት፤

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ድኅነተ ዓለም ሲል በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ለተጠመቀበት፣ ለታላቁ የአደባባይ በዓላችን ለብርሃነ ጥምቀቱ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!

“ርእዩከ ማያት እግዚኦ ርእዩከ ማያት ወፈርሁ  ደንገፁ ቀላያተ ማያት ወድምጸ ማያቲሆሙ – አቤቱ ውኃዎች አዩህ ውኃዎችም አዩህና ፈሩ ጥልቆችም ተነዋወጡ ውኃዎችም ጮሁ።” መዝ. ፸፮፥፲፮

ይህ የቅዱስ ዳዊት ቃለ ትንቢት ባሕርየ ሰብእን ለማዳን በተዋሕዶ ሰው የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሊጠመቅ በቆመ ጊዜ ግዑዛን ፍጥረታት ፈጣሪያቸውን አውቀው ያሳዩትን ድንጋጤ የሚገልጽ ነው። ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ለመጠመቅ የሄደው መጠመቅ የሚገባው ሆኖ ሳይሆን፣ እርሱ ማየ ሕይወት በመሆኑ “አፍላገ ማየ ሕይወት ዘይውኅዝ እምከርሡ – ከሆዱ የሕይወት ውኃ ወንዝ ይፈስሳል” (ዮሐ. ፯፥፴፰) ተብሎ እንደተጻፈ፤ ውኃውን ቀድሶ ለእኛ የልጅነት መገኛ እንዲሆንልን ነው።

በዚያን ዕለት ዮርዳኖስ ወደ ኋላ የሸሸውና ጥልቆች የተነዋወጡት፣ በማዕከለ ዮርዳኖስ የቆመውን የጌታችንን የባሕርይ አምላክነት ተረድተው ነው። ይህ ምስጢርም “ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ – ባሕር አየችና ሸሸች፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ” (መዝ. ፻፲፫፥፫) ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተመሰከረ፣ የሰው ልጅ የኃጢአት ዕዳ ተደምስሶ ከጨለማ ወደ ብርሃን የተሸጋገረበት ታላቅ የድል ቀን ነው።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤ ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው ለእኛ የድኅነትን መንገድ ሊከፍትልንና በጥምቀቱ የኃጢአት ዕዳችንን ደምስሶ አዲስ ሕይወትን ሊሰጠን ነው። በመሆኑም ይህን ታላቅ የድኅነት በዓል ስናከብር ክርስቶስ የከፈለንን ዋጋ እያሰብንና በጥምቀት ካገኘነው ልጅነት ጋር በሚስማማ ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር ሊሆን ይገባል። በጥምቀት ያገኘነውን ልጅነት ከሚጋርዱ፣ ከቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ሥርዓት ውጭ ከሆኑና የምስጢረ ጥምቀቱን ረቂቅነት ከሚያደበዝዙ ሥጋዊ ድርጊቶች ተቆጥበን፤ በዓሉን በሥርዓተ አምልኮ፣ በጸሎት እና መልካም ሥራዎችን በመሥራት  ልናከብረው ይገባል። 

በመጨረሻም፣ ይህ የ፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት የጥምቀት በዓል አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ የሰጠንን የልጅነት ጸጋ በሃይማኖትና በምግባር አጽንተን እንድንኖር ይርዳን። በማዕከለ ዮርዳኖስ የቆመው የባሕርይ አምላክ ለሀገራችን ሰላምን፣ ለሕዝባችንም ጤናንና በረከትን ያድልልን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

Scroll to Top