ኤክቱስ ሰኔ 14/2018 ዓ.ም
የታላቁን መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን ዓመታዊ በዓል በማስመልከት በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ዐቢይ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጠናቋል። ይህ ታላቅ ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት የተዘጋጀ መሆኑ ነው።
የዚህ መንፈሳዊ ጉባኤ ዋና ዓላማ ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ በውጪው ቅጥር ግቢ ብቻ ተመላልሰው የሚመለሱ ሳይሆን በቀጥታ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት ተካፋይ መሆን የሚችሉበትን ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑ ተገልጿል። በዚህም መሠረት የሦስቱም ቀናት የትምህርት ትኩረት ምዕመናን በጊዜ መጥተው እንዲያስቀድሱ፣ ንሥሐ እንዲገቡና ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንዲቀበሉ (እንዲቆርቡ) ለማነቃቃትና ለማስተማር ያለመ ነበር።
በጉባኤው ላይ የተገኙት ከአዲስ አበባ ድረስ የተጋበዙት መምህራን ቀሲስ ደረጀ እና መምህር ብርሃኑ አድማስ ይህንን የጉባኤውን ዓላማ መነሻ በማድረግ የምዕመናንን መንፈሳዊ ሕይወት የሚፈትሹ አስተማሪ ትምህርቶችን በጥልቀት አስተምረዋል። እንዲሁም በዝማሬ ዲያቆን ፍሬዘር ደሳለኝ እና ዘማሪት ምርትነሽ ጥላሁን አገልግለዋል።
ብፁዕነታቸው በምዕመኑ መንፈሳዊ መነቃቃት እጅግ መርካታቸውን የገለጹ ሲሆን አክለውም ለጉባኤው መሳካት በተለያየ መልኩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ምዕመናንም በንሥሐ ታጥበው የቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ተካፋይ መሆን እንዳለባቸው ባሳሰቡበት አባታዊ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የጉባኤው ፍጻሜ ሆኗል።


