በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በሀገረ ስብከቱ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችል የምክክር መድረክ ተካሄደ!

ኤክቱስ ታኅሣሥ 27/2018 ዓ.ም

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጅ ሀገረ ስብከት የሚታዩ ዘርፈ ብዙ የአገልግሎትና የአስተዳደር ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የሀሳብና የገንዘብ ድጋፍ የማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል ተካሂዷል። መርሃግብሩ በብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መሪነት በተቋቋመው መማክርት ጉባኤ አባላት የተዘጋጀ ነው። በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ ብፁዕነታቸውን ጨምሮ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞና የአሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላት ተገኝተዋል።

​ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱን የቀድሞና ወቅታዊ ሁኔታ የሚዳስስ ሰፊ የሁኔታዎች መግለጫ (Presentation) አቅርበዋል። በመግለጫውም በሀገረ ስብከቱ ሥር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሚታዩ ዋና ዋና ችግሮች የተዳሰሱ ሲሆን፣ በተለይም በገጠር አካባቢዎች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ተዘግተው መቆየታቸው ትልቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑ ተመላክቷል። እነዚህን የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት በአፋጣኝ አገልግሎት እንዲጀምሩ ማድረግ በቀጣይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑም ገልጸዋል።
​ከአብነት ትምህርት መስፋፋት ጋር ተያይዞ በሀገረ ስብከቱ ያለውን ክፍተት ለመሙላት በአሁኑ ወቅት በአንዲዳ የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት መጀመሩን ገልጸዋል። ሆኖም ግን ይህ ጅምር ካለው ስፋት አንጻር በቂ ባለመሆኑ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በስፋት ማደራጀትና በቋንቋ የሚያገለግሉ ካህናትና ዲያቆናትን ማፍራት እንደሚገባ በሰፊው አንስተዋል።

​በስብከተ ወንጌል ረገድም በአብዛኞቹ አድባራት ሰባክያነ ወንጌል ባለመኖራቸው ምክንያት ምዕመናን ተገቢውን መንፈሳዊ ትምህርት በማግኘት ላይ እንዳልሆኑ ተጠቅሷል። ይህን የስብከተ ወንጌል እጥረት ለመቅረፍና ወንጌልን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በአከባቢው ቋንቋ የሚያገለግሉ ሰባክያንን በማሰልጠንና በመመደብ ረገድ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑና ይህ በቂ አለመሆኑን በመድረኩ ላይ አንስተዋል።

​የሀገረ ስብከቱን የአስተዳደር ስራዎች ከዘመኑ ጋር ለማስማማትና የአሰራር ድክመቶችን ለማስተካከል ታሳቢ ያደረጉ የለውጥ ሀሳቦችም አቅርበዋል። የሀገረ ስብከቱ መዋቅር ይበልጥ እንዲጠናከርና ለምዕመናን የሚሰጠው አገልግሎት እንዲሳለጥ አስተዳደራዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ለውይይቱ ተሳታፊዎች አስገንዝበዋል።

​በመጨረሻም የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች በቀረቡት ዝርዝር ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ከተወያዩ በኋላ ሀገረ ስብከቱን በሁሉም ረገድ ለመደገፍ ቃል ገብተዋል። ይህም ድጋፍ በእውቀት፣ በገንዘብና በጉልበት እንደሚሆን በመግለጽ ሀገረ ስብከቱ የተደቀኑበትን ችግሮች ተሻግሮ ተልዕኮውን እንዲወጣ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

Scroll to Top