በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በሀገረ ስብከቱ የሥራ ፈጠራ ማዳበርና መሠረታዊ የንብ ማነብ ሥልጠና ተጀመረ!

ኤክቱስ

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት፤ አድባራት ከልመና እንዲላቀቁ፣ በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉና የሥራ ፈጠራ ችሎታን ለማዳበር በሥራ ፈጠራ ዙሪያ የሚያተኩር ሥልጠና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል። እስከ ጥር 20 ቀን ድረስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው ይህ ሥልጠና፤ በዲላና በወናጎ (በመንበረ ጵጵስና) ወረዳ ቤተ ክህነት ስር ለሚገኙ አድባራት ሠራተኞችና ተወካዮች ታስቦ የተዘጋጀ የዕቅድ አካል ነው።

በዛሬው መርሐግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ፣ የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች፣ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።

ይህንን ሥልጠና እየሰጠ የሚገኘው በንብ ማነብ፣ በሐር ትል እና በታዳሽ ኃይል ዙሪያ የሚንቀሳቀሰው ICIPE (International Centre of Insect Physiology and Ecology) የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በዘርፉ ያለውን የረዥም ጊዜ ተሞክሮ ለቤተክርስቲያኗ አገልጋዮችና ሠራተኞች እያካፈለ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ውሎ በሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ከዋለ በኋላ በቀጣዮቹ ቀናት ደግሞ በመሠረታዊ የንብ ማነብ ሙያ ላይ ተግባራዊ ትምህርቶች እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

የዚህ ሥልጠና ዋና ዓላማ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ የልማት መስኮች ተሰማርታ በገቢ ራሷን እንድትችል ማስቻል ነው። ይህም በቤተክርስቲያን የሚሰበሰበው “ሙዳየ ምጽዋት” ለታለመለት ለምጽዋት ተግባር እንዲውል ለማድረግ የሚረዳ መሆኑ ተመልክቷል። ተሳታፊዎችም ከሥልጠናው የሚገኘውን ዕውቀት ወደየአጥቢያቸው በመውሰድ ተግባራዊ እንዲያደርጉና የተቋሙን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ አቅጣጫ ተቀምጧል።

Scroll to Top