በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በሀገረ ስብከቱ የሕግ ክፍል ዐቢይ ኮሚቴ ብፁዕነታቸው በተገኙበት ሥልጠና ተሰጠ!

ኤክቱስ ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የሕግ ክፍል ዐቢይ ኮሚቴ አማካኝነት የተዘጋጀ የሕግ ሥልጠና ተሰጥቷል። በዚሁ መርሃግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች፣ የዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና መላው የአስተዳደር አካላት ተሳትፈዋል።

ሥልጠናውን የሰጡት የዲላ ዩኒቨርሲቲ የነጻ ሕግ አገልግሎት ማዕከል አስተባባሪ ወይዘሪት የምስራች ያለው ሲሆኑ በጠዋቱ ክፍለ-ጊዜ ስለ ሕግ ምንነት፣ ስለ ሕጋዊ ሰውነት፣ መብቶችና ስለ ንብረት ሕግ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሃ-ግብር ደግሞ ስለ ግዴታዎች፣ ውሎች እንዲሁም ስለ አሠሪና ሠራተኛ ሕጎች ትኩረት ያደረገ ትምህርት ቀርቧል። ሥልጠናው በአጠቃላይ ተቋማዊ አሠራርን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ለመምራትና መብትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የፍትሐብሔር እና የወንጀል ሕግ መሠረታዊ ነጥቦችን ያካተተ ነበር።

በሥልጠናው ወቅት ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከአሰልጣኟ በተጨማሪ የሕግ ክፍል ዐቢይ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲያቆን መስፍን ተስፋዬ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል።

በማጠቃለያው ላይ ብፁዕነታቸው በተሰጠው ሥልጠና የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው “የቤተ ክርስቲያን ሀብቷ ልጆቿ ናቸው” በማለት በበጎ ፈቃዳቸው አገልግሎት ለሰጡት ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል። አያይዘውም እንዲህ ያሉ ሥልጠናዎች ሁሉም አካል ስለ ሕግ በትክክል እንዲያውቅና ቤተ ክርስቲያንም መብቷን በሕግ አግባብ እንዴት ማስጠበቅ እንዳለባት ለማስገንዘብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመው መርሐ-ግብሩን በጸሎት ፈጽመዋል።

Scroll to Top