በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ 3558 አዳዲስ አማንያን ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት እንዲያገኙ እንዳደረገ ገለጸ!

ኤክቱስ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም

በ፵፭ኛው ዓለም አቀፍ ጠቅላላ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ የሀገረ ስብከቱን የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቀረቡ።

የቀረበው ሪፖርት በስብከተ ወንጌል አገልግሎት፣ በአብነትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ በመልካም አስተዳደር፣ በልማት፣ በዘመናዊ የፋይናንስ አሠራርና በበጎ አድራጎት ዘርፎች የተከናወኑ አበይት ተግባራትን ያካተተ ነው።

በበጀት ዓመቱ በስብከተ ወንጌል ከ22 በላይ ሕዝባዊ ጉባኤያት በአማርኛ፣ በጌዴኡፋ፣ በኮሪቴና በዳሸቴ ቋንቋዎች የተካሄዱ ሲሆን፤ ቤት ለቤት በተደረገ እንቅስቃሴ 601 ንሥሐ አባት የሌላቸው ምእመናን የንሥሐ አባት እንዲኖራቸው ተደርጓል። በማረሚያ ቤትና ሐዘን ቤቶችም አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን 21 ሰባኪያነ ወንጌል ተሠልጥነው ተሰማርተዋል። ሌላ 30 ወጣቶች ደግሞ በመሠልጠን ላይ ይገኛሉ። በዚህም 3,558 አዳዲስ አማንያን ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት እንዳገኙ ገልጸዋል።

በአብነት ትምህርት በኩል በአንዲዳ መድኃኔዓለም አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ከሚማሩት በተጨማሪ በአድባራት 1,282 ተማሪዎች በመማር ላይ መሆናቸውን ገልጸው 111 ደቀ መዛሙርት ዲቁና 19 ደግሞ ቅስና ተቀብለዋል። በተጨማሪም በማኅበረ ቅዱሳን ድጋፍ በ12 ሚሊዮን ብር በጀት የሚገነባውና 32 ተማሪዎችን የሚያስተናግደው የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ አፈጻጸም ከ60% በላይ መድረሱን ገልጸዋል። በሰንበት ትምህርት ቤት ዘርፍም የመንበረ ፓትርያርክ ሥርዓተ ትምህርት ተሰራጭቶ ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ ለ110 ወጣቶች ሥልጠና ተሰጥቶ አጠቃላይ አባላት ቁጥር 11,500 ደርሷል።

በአመራርና አስተዳደር አቅም ግንባታ በኩል ለሰበካ ጉባኤ አባላት፣ ካህናትና ሠራተኞች ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሥራ አመራርና የኮምፒውተር ሥልጠና ተሰጥቷል። የሠራተኞች ቅጥር በውድድርና በብቃት እንዲሆን መደረጉ፣ የሕግ ክፍል ዐቢይ ኮሚቴ መቋቋሙ እና በአድባራት የነበሩ ግጭቶች በውይይት መፈታታቸው ተገልጻል። በሰበካ ጉባኤ ማደራጀት በኩል የ3 አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እብነ መሠረት የተቀመጠ ሲሆን 2 የተጠናቀቁት ተባርከው አገልግሎት ጀምረዋል። በተጨማሪም 45 የስብከተ ወንጌል ኬላዎችና 14 የቤተ መቅደስ ግንባታዎች በፍጥነት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

ሀገረ ስብከቱ የአሥር ዓመት ሥልታዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን ከአሥራ ስምንት ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጀው የመንበረ ጵጵስና ግንባታ 85% ደርሷል። በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት፣ በአንዲዳ የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት እንዲሁም በአድባራት የንብ ማነብ፣ የዶሮ እርባታ፣ የግብርና፣ የኪራይ ቤቶችና የእህል ወፍጮ ሥራዎች ተጀምረዋል። በገንዘብና ንብረት አስተዳደር በኩል የደብል ኢንትሪ (Double-entry) ዘመናዊ የሂሳብ አሠራር ሙሉ በሙሉ የተተገበረ ሲሆን በዲላ ከተማ የሚገኙ አድባራት በፒችትሪ (Peachtree) ባለሙያዎች እንዲመሩ ተደርጓል። የ2017 ዓ.ም ሂሳብ ኦዲት መደረጉም ተጠቅሷል።

በሀገረ ስብከቱ ማኅበራዊ ሚዲያና ዌብሳይት ወቅታዊ መረጃዎችን ያሰራጨ ሲሆን በጌዴኦ ዞን በቡሌና ራጴ ወረዳዎች በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጓል። በፋይናንስ አቅም ግንባታ በኩል በተደረገው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የ35 ፐርሰንት ክፍያ ከባለፈው ዓመት የ47% ጭማሪ በማሳየት 4,662,462.83 (አራት ሚሊዮን ስድስት መቶ ስልሳ ሁለት ሺህ አራት መቶ ስልሳ ሁለት ብር ከሰማንያ ሶስት ሳንቲም) ገቢ ሆኗል።

በመጨረሻም ክቡር ሥራ አስኪያጁ የተሰበሰበበትን ገቢ የሚያረጋግጠውን ደረሰኝ (የባንክ ስሊፕ) ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ለብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ እንዲያስረክቡላቸው በክብር ጥሪ በማቅረብ ሪፖርቱ ተጠናቋል።

Scroll to Top