ሉቃስ ማለት በላቲኑ ትርጓሜ ብርሃናማ፣ ብርሃን የያዘ ማለት ነው፡፡ በትርጓሜ ወንጌል የተሰጠው ትርጉም ደግሞ ሉቃስ ማለት ዓቃቤ ሥራይ (ባለ መድኃኒት) ማለት ነው፣ ቀድሞ ዓቃቤ ሥራይ ዘሥጋ (ሥጋዊ ሐኪም) ነበር በኋላ ግን ዓቃቤ ሥራይ ዘነፍስ ( መንፈሳዊ ሐኪም) ሆኗልና፡፡ አንድም ተንሣኢ (ፈጣን) ማለት ነው ለስብከተ ወንጌል ይፋጠናልና፣ አንድም መበሥር (ብሥራት ነጋሪ) ማለት ነው ብሥራተ መልአክን ይጽፋልና በማለት ይተረጉመዋል፡፡የተወለደው በሶርያ አንጾኪያ ነው፡፡
አስቀድሞ ከ72ቱ አርድእት ወገን የተቆጠረ ሲሆን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወርዶ ወንጌልን ሰብኳል ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎሰ ጋር የተገናኘውም በዚሁ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ የሕክምና ሙያ የነበረው ሲሆን ያጠናውም ከአቴናና እስክንድርያ ሊቃውንት መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህ ሙያው በተጨማሪ የሥነ ሥዕል ችሎታም እንደነበረው ይነገራል፡፡ ይህንን ችሎታውንም በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ባለው ሥዕላዊ አገላለጥ ከማንጸባረቁም ሌላ በእጁ የተሳሉ ሥዕሎች በተለያዩ ሀገሮች ይገኛሉ፡፡
የቅዱስ ሉቃስ ስዕሎች እመቤታችን ልጇን አቅፋ ( ምስለ ፍቁር ወልዳ) የሳላቸው ሲሆኑ በኢትዮጵያ በተድባበ ማርያም ፤ በደብረ ዘመዶ ፤ በዋሸራ ፤በጅበላ ሲገኙ ተመሳሳዩም በስፔን ቅድስት ማርያም ካቴድራል እንደሚገኝ ይነገራል ፡፡

የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል
የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተጻፈው በሀገር አኪይያ (ሮም) በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ነው፤ የሉቃስ ወንጌል ‹የአሕዛብ ወንጌል›፣ ‹ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ›፣ ‹ሰባኬ ጸሎት›፣ ወንጌለ አንስት ተብሎም ይጠራል፡፡
፩. ‹የአሕዛብ ወንጌል› እየተባለ የሚጠራው ወንጌሉ የተጻፈው ለአሕዛብ በመሆኑ ነው፡፡
፪. ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ የሚባለው ስለ መንፈስ ቅዱስ ደጋግሞ ስለሚናገር ነው፡፡
፫. ሰባኬ ጸሎት የተባለው ከሌሎች ወንጌላት የበለጠ ደጋግሞ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ጸሎት ጽፏልና ነው፡፡
፬. ወንጌለ አንስት የሚባለው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ስለ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ ስለ ማርያም እንተ እፍረት፣ ስለ ናይን እና ወዘተ በስፋት ስለሚናገር ነው፡፡
ወንጌሉን ከመጻፉ አስቀድሞም ቅዱስ ሉቃስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ትርጓሜ ወንጌል ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በአንጾኪያ ሀገር ቅዱስ ጳውሎስን ካገኘው በኋላም ሊቀ ሐዋርያው ሰማዕት እስከሆነበት ድረስ አገልግሎታል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ጋርም በነበረበት ጊዜም መቄዶንያ የምትባል ሀገር ከፍሎ እንዲስተምር እንደሰጠው በወንጌል ትርጓሜ ተገልጿል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም በዚያ ሀገር ከጌታችን ኢየሱስ መፀነስ ጀምሮ፣ መዋዕለ ስብከቱን፣ የሠራውን ትሩፋትና ገቢረ ተአምሩን በሙሉ ለአሕዛቡ በነገራቸው ጊዜ ከኃጢያት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ተመለሰው በማመን የክርስትና ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ ለስብከት በሚጓዝበትም ወቅት ትምህርት ባልተዳረሰባቸው ስፍራ ሲያስተምር አንድ ታዖፊላ የተባለ የእስክንድርያ መኮንን ስብከቱን አድምጦ በማመን ‹ዜና ሐዋርያትን› (ገድለ ሐዋርያትን) እንዲጽፍለት በጠየቀው መሠረት ጽፎለታል፡፡ በዚህም ቅዱስ ሉቃስ የጻፋቸው መጻሕፍት ከወንጌሉና ከሐዋርያት ሥራ ጋር ሦስት ናቸው፡፡
የሐዋርያት ሥራ
የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ቅዱስ ሉቃስ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ከ1-34 ዓ.ም. ያለውን የክርስትና ታሪክ ካሰፈረ በኋላ ቀጣዩንና ከ34-58 ዓ.ም. ያለውን ደግሞ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ጽፏል፡፡
ከምዕራፍ 1-8 ያለው የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በኢየሩሳሌም የሚያሳይ ሲሆን ከምዕራፍ 9-12 ያለው ታሪክ ደግሞ በእስጢፋኖስ ሰማኝትነት በተነሣው ስደት የተበተኑት የኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ልጆች በአካባቢው ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ የሚያሳይ ነው፡፡ ከምዕራፍ 13 ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስን ጉዞዎች ተከትሎ የጻፈውና ክርስተና በታናሿ እኪያር በአውሮፓ እንዴት እንደተሰበከ የሚያሳየው ክፍል ነው፡፡
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያው የሮም እሥራቱ በቁም እሥር ላይ ሆኖ ወንጌልን እንዲሰብክ ተፈቅዶለት በነበረ ሰዓት በሮም ከሚኖሩ አይሁድ ጋር በ58 ዓ.ም ስለሃይማኖት ያደረገውን ውይይት ተርኮ ያጠናቅቃል፡፡
ወንጌላዊው ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን የጻፈው በ58/በ59 ዓ.ም/ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ዓመተ ምሕረት በኋላ የተከናወኑትን ለምሳሌ በ60 ዓ.ም የቅዱስ ጳውሎስን መፈታት ዘግይቶም በ64 ዓ.ም. የደረሰውን የሮማ መቃጠልና የአይሁድን ዓመፅ በመጽሐፉ ስላልገለጠው ነው፡፡
ቅዱስ ሉቃሰ ሐዋርያው ጳውሎስን ተከትሎ ታሪኩን ሲያሰባስብ ከኖረ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ ሲታሠር ዕረፍት በማግኘቱ አጠናቅሮ በመጽሐፍ መልክ በማዘጋጀት ለቴዎፍሎስ ልኮለታል፡፡
ሉቃሰ ዘላሕም፡- አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ቅዱስ ሉቃስ ለምን በላም እንሚመሰል ሲናገር፣ የመድኃኒታችንን መሥዋዕትነት ሐዲስዋ እምቦሳ በወለደች በንጹሕ ላም ፍሪዳ መስሎ ይናገራልና ይለዋል፡፡ እንዲሁም በከብቶች በረት መወለዱን ስለሚናገርና ታረኩም የላም ወተት ለሕፃን ልጅ ቀላል ምግብ እንደሆነ ሁሉ ለአዲሰ አማኝ ቀለል በሎ የቀረበ መሆኑን ያስገነዝባል ።
ቅዱስ ሉቃሰ የድንግልና ሕይወት የነበረው ወንጌላዊ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሰማዕትነት እስካረፈበት ጊዜ ድረስ ደቀ መዝሙር በመሆን አገልግሎታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ67 ዓ.ም. በሮማ በሰማዕትነት ሲያርፍ ሉቃስ ወደ ድልማጥያ መጣ በዚያም በሽምግልና ዘመኑ ወንጌልን በመስበክ ላይ እያለ አይሁድና ካህናተ ጣዖት ተባብረው ትምህርቱን በመቃወም ተነሡበት መስከረም 20 ቀን 68 ዓ.ም. አይሁድና አረማውያን ጉባዔ አድርገው ነገር በመሥራት ለሮም ንጉሥ ከሰሱት፡፡ በዚያን ዘመን ኔሮን እብደቱ ያየለበት ጊዜ በመሆኑ የቅዱስ ሉቃስን ከሮሜ ማምለጥና ወደ ድልማጥያ መምጣት ሲሰማ 200 ወታደሮችን ላከበት ቅዱስ ሉቃስም የሰዎችን መምጣት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ያሰተምራቸው የነበሩትን ምእመናን ወደየቤታቸው ላከና በድልማጥያ አጠገብ ወደሚገኘው ባሕር ተጠጋ በባሕሩ አጠገብ አንድ ዓሣ አስጋሪ ቆሟል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ዓሣ አስጋሪው ቀረበና ጨዋታ ጀመሩ ቀስ በቀስም ወንጌል ይሰብክለት ጀመር፡፡ ዓሣ አስጋሪውም ቅዱስ ሉቃሰ የሚነግረውን ሁሉ ሥራውን አቁሞ በደስታ ያዳምጠው ነበር በመጨረሻ እንካ እነዚህ የሕይወትን መገንድ ይመሩሃል አለና የያዛቸውን መጻሕፍት ሁሉ ሰጠው ያም ዓሣ አስጋሪ እጅግ ተደስቶ ዕቃ በሚያስቀምጥበት ቦታ በክብር አኖራቸው ቅዱስ ሉቃስ መጽሐፉን ሰጥቶት ዘወር ሲል የኔሮን ወታደሮች ተረባረቡና ያዙት ከዚያም ወደሮም ተወሰደና የኔሮን ፍርድ ቤት ቀረበ ።
ንጉሡ ‹‹በሥራይህ ሕዝቡን የምታስት እስከ መቼ ነው?›› ብሎ ጠየቀው፤ ቅዱስ ሉቃስም ‹‹እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም›› ብሎ መለሰለት፡፡ ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው፤ ‹‹እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይህች እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ በቆረጡትም ጊዜ ‹‹ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ ዕወቅ፤ ነገር ግን የጌታዬና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ፤›ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት፤ ከዚህም በኋላ ለያት፤ በዚያም የነበሩ አደነቁ፤ የሠራዊቱም አለቃና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ፡፡ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ በማዘዙ ቆረጡአቸው፤ የምስክርነት አክሊልም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ያረፈው በ፹፬ ዓመቱ ነው፡፡
ከዚህም በኋላ ሥጋውን በማቅ አይበት ውስጥ አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት፤ በአማረ ቦታም አኖሩት፡፡
የወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ አማላጅነት፣ ተረዳኢነትና በረከት አይለየን፤ አሜን!
መልአከ ብርሃን ዳንኤል ነቢዩ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ኃላፊ፣ የዳግማዊት ጌቴሴማኒ በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ