ይህን የመዘገበልን ቁጥሩ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የሚመደበው ከአራቱ ወንጌላውንም አንዱ የሆነው፣ "የተወደደው ባለመድኃኒቱ "እያለ ቅዱስ ጳውሎስ የሚጠራው ቅዱስ ሉቃስ ነው።ቆላ 4፥14
እስጢፋኖስ ማለት አክሊል (ዘውድ)ማለት ነው።
በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሀገረ እስራኤል ተወልዷል።አባቱ ስምዖን እናቱ ሐና ይባላሉ። መጀመሪያ ከመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በኋላም ከቅዱሳን ሐዋርያት ተምሯል። የመልካም ዛፍ መልካም ፍሬ ለመሆን የበቃ መንፈሳዊ ወጣት ነበር። ማቴ7፥17
በምእመናን ዘንድ መታመንንና መወደድን ያተረፈ፣ በወጣትነት ጊዜው በመንፈሳዊ ዕውቀትና በመንፈሳዊ ጥበብ ያደገ ፣በሃይማኖት የጸና፣
መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ነበር። በአንደኛው መቶ ከፍለ ዘመን ማለትም ከ34-41 ዓ/ም ባለው ጊዜ አይሁድና አሕዛብ ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላ በመካከላቸው መነቃቀፍ ፣መተማማትና አለመግባባት ተፈጥሮ ጉዳዩ ከሐዋርያት ሲደርስ “ኢይደልወነ ከመንኅድግ ቃለ እግዚአብሔር ወንፀመድ ማዕዳተ – የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ አይገባንም” ሐዋ 6፥2 ብለው ችግሩን የሚፈቱ፣ በመልካምነታቸው የታወቁ፣ መንፈስቅዱስ የሞላባቸው፣ ጥበበኞች የሆኑ ሰባት ሰዎች እንዲመረጡ በማዘዛቸው ችግሩን እንዲፈቱ በሕዝቡ ተመርጠው በሐዋርያት ከተሾሙት 7 ዲያቆናት አንዱና ዋናው ነበር። በመሆኑም ሊቀ ዲያቆናት (የዲያቆናት አለቃ) ይባላል። የሐሥ 6፥6 ይሄ ምን ይነግረናል? ሐዋርያት መርጠው እንሹባችሁ አላሉም ።ሕዝቡን ራሳችሁ ምረጡ አሏቸው እንጂ። ይህ ነገርም ሕዝቡን ደስ አሰኝቷል። የአመራረጡ መስፈርት መልካምነት፣ ጸጋ መንፈስ ቅዱስና ጥበብ እንጂ ዝምድና አልነበረም ቀረቤታ አልነበረም ብሔር አልነበረም ቋንቋም አልነበረም እጅ መንሻሞ አልነበረም ጆሮ ጠቢነትም አልነበረም አማላጅም አልነበረም ጮሌነትም አልነበረም። በዚህ ሁሉ የመጣ(የተሾመ)ችግር ከማባባስ ባለፈ ችግር ፈቺ መሆን አይችልም ሰው ያለ ቦታው ተቀምጦ እንዴት ችግር ሊፈታ ይችላል? ለመንፈሳዊ ሹመት መንፈሳዊ ሰው ነው የሚገባው የዛሬዋ ቤተክርስቲያን ከዚህ ምን መማር አለባት ? በሊቀ ዲያቆንነቱ ጊዜ 8000 ማኅበረ ክርስቲያንን መርቷል። በአገልግሎቱ ኦሪት እጠፋ እጠፋ ፣ወንጌል እሰፋ እሰፋ ብላለች። በእኛ የአገልግሎት ጊዜ ክርስቲያንነት እሰፋ እሰፋ፣ ኢክርስቲያንነት እጠፋ እጠፋ ብሎ ይሆን??
በእስጢፋኖስ የአገልግሎት ጊዜ ናዖስ የሚባል መሠርይ (ጠንቅዋይ) (ጠንቋይ) በምትሐታዊ ተአምራት ሕዝቡን ሲያስት እውነተኛ ተአምራትን በማድረግ የናዖስን የምትሐት ሐሰትነትና ከንቱነት ለሕዝብ በማሳየት በእምነቱ እንዲጸና፣በምትሐታዊ ተአምር ከመታለል ራሱን እንዲጠብቅ በማስተማር የዕቅበተ እምነት ተልእኮውን በሚገባ ተወጥቷል። መሠርዩ ናዖስ በምስሐበ አጋንንትወደሰማይ ዐርጋለሁ ሲል በስመ እግዚአብሔር አውርዶ መሬት ላይ የጣለ
ገባሬ ተአምራትም ነው ይባላል።የሐሥ6፥8
የሄኖክን የትውልድ ሱባኤ፣
የዳንኤልን የሰንበት ሱባኤ
የኤርምያስን የዕለት ሰባኤ አውጥቶ
ኦሪትን ከወንጌል፣ዘመኑን ከዘመን ፣ትንቢቱን ከመድኅን አስማምቶ ዘመነ ሥጋዌ እንደደረሰ፣እግዚአብሔር ወልድ ሥጋ እንደለበሰ ሲያስተምር”ወሰእኑ ተቃውሞቶ”እንዲል እስጢፋኖስ የሚናገርበትን ጥበብ መቃወም ቢሳናቸው ተበሳጭተው ወደ ዐደባባይ አውጥተው በደንጊያ ወግረው ገድለውታል።እርሱም ሰማዕትነትን ተቀብሏል።
ቀዳሜ ሰማዕት ይባላል።የሐዲስ ኪዳን ሰማዕታት መጀመሪያ ማለት ነው።”በእስጢፋኖስ አዕባን እመየኀልቁ፣ወገረኒ ኢያሱ በወርቁ”እንዳለ ባለቅኔው።ኦሪትን በሥርዓተ መላእክት ተቀብያለሁ ብሎ የሚመጻደው፣ነገር ግን ኦሪት የማይጠብቀው የአይሁድ ጉባኤ”ኦሪት ከወንጌል፣ዘመን ከዘመን፣ትንቢቱ ከመድኅን”እንደማይገጥም ለማሳየት ሲሉ
ዓመተ አበውን ለመቀነስ፣ኦሪተ ሌዋውያንን ወደ ኦሪተ አይሁድ ብጡል ለመለወጥ ተገዷል ። “ከሸንጎ ቢረታ ሚስቱን ከቤት መታ” እንደሚባለው ማለት ነው።”እሙንቱሰ እምከንቱ ውስተ ከንቱ”እንዲል አካሔዱም ከጥፋት ወደፋት ሆኖበታል። እስጢፋኖስን እንጂ የእስጢፋኖስን እምነት መግደል አልቻለም “ዛሬም ክርስታያኑን እንጂ ክርስትናን መግደል አይቻልም።ማጥፋት አይቻልም ።መከራ ሊኖር ይችላል።ስደት ሊኖር ይችላል ፣ጫና ሊኖር ይችላል ነገር ግን ክርስቲያንነት ድል ያደርጋል እንጂ ድል አይሆንም።አይሸነፍም። ቅዱስ እስጢፋኖስ ግን “እግዚኦ ስረይ ሎሙ ዘንተ ኀጢአቶሙ ወኢትረሲ ቦሙ ጌጋየ” አቤቱ ይሄን በደል አታድርግባቸው” የሐሥ7፥60 በማለት ከክርስቶስ የተማረውን ይቅር ባይነትን ሉቃ 23፥34 ገዳዮቹን ይቅር በማለትና “ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመጠዋ ለነፍስየ” ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል” የሐሥ 7፥59
ከርስቶስን መስሎታል ሉቃ23፥46 1ኛ ቆሮ 11፥1
“በዚያን ጊዜም በቤተክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ” የሐሥ 8፥1 ማኅበረ እስጢፋኖስ ወደ እስያ ወቢታንያ ወደ ቀጰዶቅያ ተበትኗል።ይህም ውስጡ ጥበበእግዚአቦሔር ነበር በኢየሩሳሌም በኖሩ ሃይማኖት ይጸናል እንጂ አይሰፋም ነበር አሁን ግን ወንጌልን
በደረሱበት ሥፍራ ሁሉ ስለሰብኩ የሃይማኖት መጽናት ብቻ ሳይሆን መስፋትም ሆነ።
“እግዚአብሔርን ለሚወዱት እንደ ዐሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን” ሮሜ 8፥28
ጥቅምት 17 ሢመቱ ጥር 1 ዕረፍቱ
የሰማዕቱ ረድኤትና በረከት አይለየን።
ሊቀ ማእምራን ሰሎሞን ፈጠነ
