ኤክቱስ ታኅሣሥ 5/2018 ዓ.ም
በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት በቆቲ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቅድመ ጥምቀት መደበኛ ትምህርት ከተማሩ አንድ መቶ አርባ ዘጠኝ ንዑሰ ክርስቲያን መካከል ሰባ ስምንት ወንድ እና ስድሳ ሦስት ሴት በድምሩ አንድ መቶ ሠላሳ ሁለቱ በዛሬው ዕለት በብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል።
ኢ-አማንያን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱና የሥላሴን ልጅነት እንዲያገኙ ማድረግ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ተልእኮ ከመሆኑ አንጻር ሀገረ ስብከቱ ይህንን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እያስፈጸመ ይገኛል።
አዳዲስ አማንያንን የማስጠመቁን ሥራ የደብሩ ስብከተ ወንጌል ከደብሩና ከወረዳ ቤተ ክህነቱ ጋር በመናበብ የተሠራ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ አስራ ሰባት አዳዲስ አማንያንን ለማስጠመቅ ቅድመ ዝግጅታቸውን መጨረሳቸውን ገልጸዋል።
በዕለቱ የዕለቱን ትምህርት የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ በጌዴኡፋ ቋንቋ አስተምረዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው በጌዴኡፋ እና በአፋን ኦሮሞ ዝማሬ ዘምረው እንዲሁም አዳዲስ የተጠመቁ ምዕመናንን ማጽናት እንደሚገባ ገልጸው በአፋን ኦሮሞ እና በአማርኛ ቋንቋዎች ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው በጸሎት ፈጽመዋል።
በመርሃግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ የመንፈሳዊ ትምህርትና የካህናት አገልግሎት ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ምሕረቱ፣ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን እሸቱ ማሞ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ምዕመናን ተገኝተዋል።
