ኤክቱስ ታኅሣሥ 7/2018 ዓ.ም
ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሀገረ ስብከቱን የፋይናንስ አስተዳደር ለማሻሻል የሚያስችል ውይይት ከአስተዳደር አካላት ጋር አደርገዋል። የውይይቱ ዋና ትኩረት የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ሲጠቀምበት የቆየውን ድርብ የሒሳብ አመዘጋገብ (Double-Entry Accounting) ሥርዓት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተግባራዊ ማድረግ ላይ ነበር።
የሀገረ ስብከቱ የፕሮጀክት ማናጀር ቀሲስ ጤናው እንዳላማው ስለ ድርብ የሒሳብ አመዘጋገብ (Double-Entry) አስፈላጊነት ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል። ይህ ሥርዓት እያንዳንዱ ገንዘብ በሁለት የሒሳብ መዝገቦች መመዝገብ እንዳለበት የገለጹ ሲሆን ይህም የሒሳብ ስህተቶችን ለመቀነስ እና የገንዘብ አያያዝን ሚዛናዊ (Balanced) ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የአስተዳደር አካላት ሀገረ ስብከቱ ይህንን ዘመናዊ ሥርዓት ወደ አድባራት ለማውረድ እየሠራ ያለው ሥራ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ በአግባቡ እና በግልጽነት ማስተዳደር እንዲቻል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹ ሲሆን ሥራውን ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ይህንን የዘመናዊ የሒሳብ ሥራ በብቃት ለመምራት የሚያስችል የሰው ኃይልን ለማጠናከር በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ የተመረቀ እና የሒሳብ ሥራዎችን በብቃት ለመሥራት የፒችትሪ (Peachtree) አመዘጋገብ ሶፍትዌር ዕውቀት ያለው ሰው እንዲቀጠር ተወስኗል። ይህ ቅጥር ሀገረ ስብከቱ በፋይናንስ አያያዝ ሂደት ግልጽነትን እና የሥራ ቅልጥፍናን ለማምጣት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተገልጿል።
በውይይቱ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ፣ የሀገረ ስብከት የክፍል ኃላፊዎች፣ የመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና ጸሐፊ፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የአስተዳደር አካላት ተገኝተዋል።
