በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ብፁዕ አቡነ ገሪማ በምሥራቅ አርሲ የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ!

ኤክቱስ የካቲት 22/2018 ዓ.ም

“ወተዓገሱ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት – ስለመንግሥተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ”

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ

​በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ኦርቶዶክሳውያን በታጣቂዎች በግፍ መገደላቸውን እና ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ስንሰማ እጅግ ከፍተኛ ኀዘን ተሰምቶናል።

​ቀደም ሲልም በዚሁ ዞን በኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚፈጸመውን ግድያ በመቃወም የኀዘን መግለጫ መስጠታችን የሚታወስ ቢሆንም ድርጊቱ ዛሬም በባሰ ሁኔታ ተደግሞ ንጹሐን ደማቸው መፍሰሱ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ነው።

በመሆኑም በሀገረ ስብከቱ በተለያዩ ጊዜያት በኦርቶዶክሳዊያን ልጆቻችን ላይ የሚፈጸመውና የተፈጸመው ዘግናኝና እጅግ አሳዛኝ ግድያዎች የኦርቶዶክሳዊያን ልጆቻችንን በየትኛውም የሀገራችን ክፍል በነጻነት የመኖርና ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የመፈጸም መብትን የሚጋፋ በመሆኑ የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ መከታተልና የማያዳግም መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ መፈለግ እንዳለባቸው እያሳሰብን፤ የሚመለከተው አካልም የአካባቢው ችግር ከሥር መሠረቱ እስከሚፈታ ድረስ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማሳሰብ እንወዳለን።

​በመጨረሻም በዚህ ዘግናኝና አሳዛኝ ግድያ ሕይወታቸውን ላጡ ልጆቻችን እግዚአብሔር አምላክ መንግሥተ ሰማያትን እንዲያወርስልን እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጥልን የቅድስት ቤተክርስቲያናችን የዘወትር ጸሎቷ መሆኑን እንገልጻለን።

እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ!

አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስ
የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

Scroll to Top