ኤክቱስ የካቲት 3/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ከጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተጠናቋል። መርሃ ግብሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅራዊ አሠራር ለማዘመንና አገልጋዮችን በዕውቀት ለማነጽ ታቅዶ የተከናወነ ነው።
በሥልጠናው ወቅት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ልዑክ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ስለ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አደረጃጀት፣ ስለ ቃለ ዐዋዲ አፈጻጸም እንዲሁም ስለ ሥራ ክንውንና ሪፖርት አቀራረብ፣ ስለ ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና ስለንብረት አስተዳደር ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል። መልአከ ምሕረት አምሃ መኳንንት በበኩላቸው ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅርና አሠራር ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ ማስጨበጫ አቅርበዋል።
ሠልጣኞቹ በቀረቡት በእነዚህ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችንና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማንሳት ከአሰልጣኞቹ ጋር ሰፊ የሃሳብ ልውውጥ አድርገዋል። ይህ የውይይት መድረክ በንድፈ ሐሳብ የተሰጠው ሥልጠና በተግባር ካለው አሠራር ጋር እንዲዛመድ ትልቅ እገዛ ማድረጉ ተገልጿል።
በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ የሰልጣኞችን ዝግጁነት የሚያሳይ አጭር የአቋም መግለጫ ቀርቧል።
በመጨረሻም በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ ጋባዥነት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ባስተላለፉት አባታዊ ቃለ ምዕዳን ሠልጣኞች በውይይቱና በሥልጠናው የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ በታማኝነት እንዲወጡ አሳስበዋል። በተጨማሪም ለሥልጠው መሳካት አስተዋጽዖ ላደረጉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ምሥጋናቸውን አቅርበው መርሐ ግብሩን በጸሎት ፈጽመዋል።
