ኤክቱስ የካቲት 2/2018 ዓ.ም
በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መሪነት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪና የኢቢሲ ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት በሀገረ ስብከቱ የሚከናወኑ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በመጀመሪያነት የተጎበኘው በአንዲዳ የሚገኘው የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ሲሆን፤ የመማር ማስተማር ሂደቱ፣ የአብነት ትምህርት ቤቱ ራሱን ለማስቻል ከሚሠሩ የግብርና ሥራዎች መካከል የዶሮ ፕሮጀክት፣ እንዲሁም የመማርያ፣ የመመገቢያ፣ የማደርያ እና የጽሕፈት ቤት ክፍሎች ተጎብኝተዋል። በመቀጠልም በዳማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው የእንሰት ልማትና የንብ ማነብ ሥራዎች የተጎበኙ ሲሆን፤ ሀገረ ስብከቱ የሚያስገነባው የመንበረ ጵጵስና ሕንጻ ግንባታም ተመልክተዋል።
በመጨረሻም በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሚሠሩ የውኃ እና የዶሮ ፕሮጀክቶችን የጎበኙ ሲሆን፤ ክቡር ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ ቤተክርስቲያኗ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግና ራሷን ለመቻል እያከናወነች ያለችውን ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴ አድንቀዋል።
