በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

‎”በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ” (ሐዋ 6:3)‎በዚህ የአባቶቻችን የሐዋርያት መመሪያ መሠረት ከተመረጡ አገልጋዮች መካከል አንዱ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ነው።

በመጋቤ ምሥጢር ጥበቡ አናጋው

ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ እግዚአብሔር ልኮት ኢትዮጵያዊውን ጃንረባ ባኮስን ያጠመቀው ነው።

‎የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታረክ፣ ምስረታ እና ልደት የሚያወሳ የታሪክም ሆነ የቤተክርስቲያን ምሁር ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስን እና ቅዱስ ባኮስን ሳያነሳ ማለፍ አይቻለውም፡፡

‎ምክንያቱም በኢትዮጵያ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንዲሰበክ መነሻ የሆኑ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የወንጌል አባታቶቻችን ስለሆኑ ነው፡፡

‎ከሰባቱ ሊቃነ-ዲያቆናት አንዱ ሆኖ የተሾመው ቅዱስ ፊልጶስ ትውልዱ ኢሲዶር ከምትባል የቄሳሪያ የወደብ ከተማ ሲሆን በቅዱስ እስጢፋኖስ ሞት ምክንያት ደቀመዛሙርት ከኢየሩሳሌም እስከተበተኑ ድረስ በኢየሩሳሌም ከሐዋርያት እግር ስር ሆኖ ተምሯል፡፡

‎ከመንፈስ ቅዱስ መገለጥ በኋላ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ባደረጉት የመጀመሪያ የስብከት አገልግሎት በርካታ ምዕመናን አምነው ተጠመቁ፤ የምዕመናኑ ቁጥር እጅግ በመጨመሩ እና የአገልግሎቱ ዘርፉም እየበዛ በመሄዱ አገልጋዮችን መጨመር አስፈላጊ መሆኑን ባመኑ ጊዜ ሐዋርያት ቀደም ሲል በአርድትነት ሲያገለገሉ ከነበሩት መካከል ሰባቱን ሊቃነ-ዲያቆናት ለመጋቢነት መረጡ፡፡

‎ምዕመኑን በመጋቢነት እንዲያገለግሉ ከተመረጡት ሰባቱ ሊቀ-ዲያቆናት መካካል አንዱ ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ ዘሰማርያ ወኢትዮጵያ ነው፡፡

‎በ35ዓ.ም. ቅዱስ እስጢፋኖስ በአይሁድ እጅ በሰማዕትነት ማለፉ ተከትሎ በኢየሩሳሌም የነበሩት ማኅበረ ምዕመናን ተበተኑ፤ ቅዱስ ፊልጶስም ጊቶን ወደ ምትባል የስሞን መሠርይ የትውልድ ስፍራ ወደሆነች የሰማርያ ከተማ ሄደ፡፡

‎በዚያም ሐዋርያዊ አገልግሎቱን በማጠናከር በርካታ ምዕመናን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምነው እንዲጠመቁ አስችሏል፡፡ በተለይ በጥንቆላ ግብሩ የሚታወቀውን ሲሞን መሠርይን በማሳመን ማጥመቁን ቅዱስ መጽሐፍ ዘግቦለታል፡፡ ሐዋ 8፡13።

‎በሰማርያ ሳለ የጌታም መልአክ ፊልጶስን ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ አለው፡፡ እርሱም ተነሥቶ ሂደ፡፡ እነሆ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባላሟል እና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘ፡፡

‎ይህም ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፡፡ ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡ መንፈስም ፊልጶስን “ሂድ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው፡፡ ፊልጶስም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ሂደ፤ ጃንደረባውም የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰምቶ “ለመሆኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው፡፡ ጃንደረባውም “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውለዋለሁ” አለው፤ ቅዱስ ፊልጶስም ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሰበከለት፡፡ በመጓዝ ላይ ሳሉም ውሃ ካለበት ስፍራ ደረሱ ጃንደረባውም “እነሆ ውሃ እዚህ አለ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው፡፡ ፊልጶስም “በፍጹም ልብህ ካመንህ መጠመቅ ትችላለህ” አለው፡፡ ጃንደረባውም ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ›› ሲል መለሰለት፤ ሠረገላውም እንዲቆም አዘዘ፡፡

‎ከዚያም ሁለቱም አብረው ወደ ውሃው ወረዱ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው፡፡ ከውሃውም በወጡ ጊዜ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጥቆ ወደ አዛጦን ወሰደው። ሐዋ 8፣ 26-39። ወደ ቂሣርያ እስኪመጣ ድረስም በእየከተሞቹ ሁሉ እየተዘዋወረ ወንጌልን ሰብኳል፡፡ በቂሳርያ ሳለ ሚስት አግብቶ 4 ሴቶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው ደናግናል ነበሩ፡፡ ሐዋ 21፣8። በረጅም የወንጌል አገልግሎቱ ብዙ አይሁድን እና ሳምራዊያንን ወደ ክርስትና መልሶ ጥቅምት 14 ቀን በሰላም ማረፉን የታረክ መዛግብት ይናገራሉ፡፡

‎የሐዋርያው የቅዱስ ፊሊጶስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!

መጋቤ ምሥጢር ጥበቡ አናጋው

ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም

Scroll to Top