ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ‼️
ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያና ወንጌላዊ እንዲሁም ሰማዕት ነው፡፡ ከዚህም ጋር የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን መሥራች አባት ነው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ኢየሩሳሌም ውስጥ ክርስቲያኖች በቤቷ ለጸሎትና ለትምህርት ይሰበሰቡ የነበረችው የማርያም ልጅ ሲሆን አባቱ አርስጦሎስ አጎቱ በርናባስ ነበሩ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ሁል ጊዜ በእናቱ ቤት እየተሰበሰቡ ጸሎት በማድረግ ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑ ነበር፡፡ « ማርቆስ በተባለ ዮሐንስ ቤት ሐዋርያት ይጸልዩ ነበር፡፡ »(የሐዋ 12፡12) እናቱ ማርያም እጅግ የከበረች ባለጸጋ እንደነበረችም በመጸሐፈ ስንክሳር ተገልጿል፡፡
ቅዱስ ማርቆስ በትውልዱ ዕብራዊ ሲሆን ቤተሰቦቹ ግን ይኖሩ የነበሩት ሲረኒካ በተባለችውና በዛሬዋ ሊቢያ ምዕራባዊ ጠረፍ በተቆረቆረችው ከተማ ነበር። ነገር ግን የሰሜን አፍሪቃ ዘላን ጎሳዎች በየጊዜው በከተማው ጥቃት እየሰነዘሩ ቤተሰቦቹን አላስቀምጥ ስላሏቸው ወደ ትውልድ ሀገራችው ኢየሩሳሌም በመመለስ ቤት ሰርተው ተቀመጡ።
ቅዱስ ማርቆስ በመጀመሪያ ስሙ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራ ነበር እናቱም ልጇን ማርቆስን የዕብራይስጥና የዮናናውያን ቋንቋ አስተምራው ነበር ፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በወጣትነት ዘመኑ የጌታን ትምህርት ሰምቶ ልቡ ስለተነካ ሁሉን ነገር ትቶ የክርስቶስን ወንጌለ መንግስት ሰማያት ለመስበክ ቆርጦ ተነሳ ጌታ ካረገ በኋላ ቅዱስ ማርቆስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በመሆን ወንጌልን በማስተማሩ ቅዱስ ጴጥሮስ ልጄ እያለ ይጠራዋል፡፡(1ኛ ጴጥ 5፡12) ባሕረ ጥበባት ቅዱስ ያሬድ ስለዚህ ታላቅ ወንጌላዊ ተጋድሎ ሲመሰክር እንዲህ ብሏል ፡- « ወአንተሰ ትልወኒ በትምህርትየ ወበግዕዝከ ዘመሀርኩከ አስተፋጥን ትሬሲ ርእስከ ኅሩየ ለእግዚአበሔር ማርቆስ ክቡር ወንጌላዊ ዐቃቢሁ አንተ ለልዑል ድርገተ ኮንከ እንተ ላዕለ ኀይል ብእሴ እግዚአብሔር አንተ ግን በትምህርቴና በጠባይህ ተከተለኝ ያስተማርኩህን አፋጥን ለእግዚአብሔር ራስህን የተመረጥክ ታደርጋለህ ክቡር ወንጌላዊ ሆይ አንተ የልዑል ጠባቂ (አገልጋይ) ነህ የእግዚአብሔር ሰው ማርቆስ ሆይ በኀይል ላይ አንድነትን የያዝክ ሆንከ » በማለት መስክሮለታል፡፡
ማርቆስ ማለት ንህብ ማለት ነው፡፡ ንህብ ሁሉን እንደሚቀስም እሱም ቀድሞ ከክርስቶስ ኋላ ከሐዋርያት ተምሯልና፡፡ አንድም ልዑክ ማለት ነው፡፡ ለስብከተ ወነንጌል ይፋጠናልና፡፡ ማርቆስ አንበሳ ማለት ነው፡፡ አንበሳ ለላም ጌታው ነው ይሰብረዋል እሱም በግብጽ አምልኮተ ጣዖትን አጥፍቷልና፡፡
ሐዋርያት ይህን ዓለም ዕጣ በጣ ብለው ተካፍለው ለማስተማር በሚወጡበት ጊዜ ለቅዱስ ጴጥሮስ ሮም በዕጣ ደርሳዋለች በተደራቢነትም ግብጽም ደርሳዋለች፡፡ ለአርእድት ግን ዕጣ የላቸውም አንዱም ሁለቱም እየሆኑ አንዱን ሐዋርያ አንዱም ሁለቱም አንዱን ሐዋርያ ተከትለው ሄዷል ግብጽን ለማርቆስ ሰጥቶት እሱም ሮም ወርዷል፡፡
ማርቆም ከዚህ ገብቶ ጌታ ከጽንስ ጀምሮ ያደረገውን ታምራት ያስተማረውን ትምህርት የሠራውን ትሩፋት ቢነግራቸው ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመለሱ አመኑ ተጠመቁ፡፡
“ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር ጎበዛዝቱም ያዙት እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ።” (የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 14፡51) በአራቱ ወንጌል ላይ ስለ ቅዱስ ማርቆስ የተነገረው ቃል ይህ እንደሆነ በብዙዎች ሊቃውንት ዘንድ ይታመናል፡፡
ቅዱስ ማርቆስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀመዝሙር እንደነበረ በኋላም ከአጎቱ ከበርናባስ ጋር እንዳገለገለ ቅዱሳት መጽሐፍት ይመሰክራሉ፡፡ ” በርናባስም ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይወስድ ዘንድ አሰበ፤” (የሐዋርያት ሥራ 15:37)
ቅዱስ ማርቆስ በአንጾኪያ በርናባስን እያገለገለ አስተምሯል፡፡ (የሐዋርያት ሥራ 12:25) በርናባስ ካረፈ በኋላ ወደ ሮሜ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘንድ ሄዶ ለእርሱ ደቀመዝሙር ሆነ፡፡ ጴጥሮስ የተረጎመለትን ወንጌል በሮሜ አስተመምሯል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከፍጹምነት መብቃቱን አውቆ ጵጵስና ሾሞ ከሀገረ ስብከቱ ግብጽን ከፍሎ አስተምር ብሎ ሰጥቶታል ባሕረ ጥበባት ቅዱስ ያሬድ ታሪኩን በዜማ ሲገልጠው እንዲህ ብሏል ፡-« ወረደ ጴጥሮስ ሐቂፎ መንበሮ ለቅዱስ ማርቆስ ወይቤሎ አባ አባ ባርከኒ ብእሲ ወንጌላዊ ዘኩልነ አብ ውስተ ኩሉ ግብፅ አድሚያሃ በስብከትከ ወንጌላዊ ፡፡» ጵጥሮስ የቅዱስ ማርቆስን ዙፋን አቅፎ ወረደ አባት ሆይ የሁላችን ወንጌላዊ ሰው ባርከኝ በስብከትህ በግብፅ በአውራጃዋ ሁሉ ላይ አሰማሁ፡፡
ቅዱስ ማርቆስ በስሙ የሚጠራ ወንጌል ጽፏል ቁጥሩም ከ72ቱ አርዕድት ነው፡፡ ወንጌል የሰበከውም በሰማዕትነት ያለፈው በግብፅ ነው፡፡ ክርስትናን በግብፅ የሰበከ ብዙ ተጋድሎ ያደረገ ድንቅ አባት ነው። ቅዱስ ማርቆስም በቤቱ የጌታን ትምህርት ሰምቶ ልቡ ስለተነካ ሁሉንም ነገር ትቶ የክርስቶስን ወንጌለ መንግሥተ ሰማያት ለመስበክ ቆርጦ ተነሳ፡፡ በተጨማሪም የአባቱን እህት ቅዱስ ጴጥሮስ ስላገባት ከእርሱ ጋር በቀላሉ ለመተዋወቅ ችሏል። ጌታ ካረገ በኋላ ሐዋርያት ዓለምን በዕጣ ተከፋፍለው ሲወጡ ከሐዋርያው ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር በመጀመሪያው ጉዞ በ46 ዓ.ም ለስብከተ ወንጌል ወጥቶ ነበር። ነገር ግን እናቴ ናፈቀችኝ ብሎ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ከዚያም ከሐዋርያው ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር መኖር ጀመረ። ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በመሆን በታናሿ እስያ አድርገው እስከ ሮም ድረስ ወንጌልን አስተምረዋል።
