eotc site

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን
የጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጅ ሃገረ ስብከት

የአባ ገሪማ መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሃገረ ስብከት ለምትገኙ
የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ!

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ።

የሰው ልጅ በኀጢአተኛዎች እጅ ዐልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው። (ሉቃ 24፡6-7)

የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ ሳይሆን
አስቀድሞ በነቢያት የተነገረ በተለይም በዳዊት “እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ” (መዝ 77፡
68) ተብሎ እንደሚነሣ በእርግጠኛነት የተነገረለት፤ በሆሴዕ ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ ሞት ሆይ
ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ ማጥፋትህ ወዴት አለ? (ሆሴ 13፡14) ተብሎ ለአምስት ሺህ አምስት
መቶ ዘመን እንደ መዥገር በሰው ልጅ ተጣብቆ የኖረውን የሞት ኃይል አድቅቆ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን
እንደሚነሣ ያለጥርጥር የተነገረና እውነት የሆነ ትንቢት ነበር። ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሰ
አንበሪ ማደሩ (ት ዮናስ 2፡1) ክርስቶስ በመቃብር ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት አድሮ በኃይል
እንደሚነሣ በምሳሌ የተነገረና በሙሉ ተስፋ ሲጠበቅ የኖረ ትንሣኤ ነው። ትንቢቱን አውቆ ያናገረ
ምሳሌውንም እንዲሁ አውቆ ያስመሰለ ጌታ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በምድር ላይ ዞሮ ባስተማረበት
ወቅት ከመሞቱ አስቀድሞ ገና በገሊላ ሳለ “የሰው ልጅ በኀጢአተኛዎች እጅ ዐልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል
በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው” (ሉቃ 24፡67፤ ማቴ. 12፡40) ተብሎ የተነገረው ትንቢትና
የተመሰለው ምሣሌ እሙን ሊሆን መቅረቡን በአንደበቱ አበክሮ ለደቀ መዛሙርቱ ሲያሳስባቸውና
ሲያስታውሳቸው የነበረ የድል አድራጊነት ትንሣኤ ነው።

በመሆኑም ዕለቲቱና ሰዐቲቱ በደረሰች ጊዜ በጥቂት ጥቅመኛ ነገረ ሰሪዎች ከውጭ በነ ሃናና ቀያፍ ከውስጥ
ደግሞ በነ ይሁዳ አማካኝነት ለሞት ተላልፎ ተሰጠ። በዕለተ ሆሣዕና “ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት” ሲል
የነበረው ሕዝብ ይሰቀል ይሰቀል እያለ እንዲጮኽ የሀሰት ወሬ በከተማው ሁሉ ተነዛ። ጲላጦስም ምንም
የሰራው ወንጀል እንደሌለ እያወቀ ከሥልጣኑ እንዳይሻር በመስጋት የሕዝቡን ጩኸት ፈርቶ እንዲሞት
ፈረደበት። በአይሁድ ዘንድ እንደወንጀለኛ መቆጠሩና በነሱ እጅ መሞቱ ግን በነቢዩ በኢሳይያስ “ስለ
መተላለፋችን ቈሰለ ስለ በደላችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በርሱ ላይ ነበረ በርሱ ቊስል እኛ
ተፈወስን” (ኢሳ 53፡5) ተብሎ የተጻፈው ይፈጸም ዘንድ ነው። ዓርብ በዘጠኝ ሰዐት ራሱን ዘንበል አድርጎ
ነፍሱን በገዛ ፈቃዱ ሰጠ። ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት።

የሃናና ቀያፋ ሴራ ግን በመግደል ብቻ አላበቃም ትንሣኤውን ለመከልከል ካልሆነም እነሣለሁ ብሎ
የተናገረው እውነት ሆኖ ከተነሣ እኛ ተኝተን ሣለን ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሰርቀው ወሰዱ የሚለውን
የተለመደ የሽብርና የሀሰት ወሬ ለመንዛት እንዲመቻችው መቃብሩን በወታደር አስጠበቁ።

የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ!

የኛ ጌታ ግን ሀሰተኞችንና የሀሰት አባቷ የሆነውን ዲያብሎስን ለማሳፈር፣ የሞትን ኃይል ባዶ ለማድረግና
ነቢያት ስለ ትንሣኤው አስረግጠው የተናገሩትንና እርሱም እንደሚነሣ ከሞቱ አስቀድሞ ስለራሱ
የተናገረው የትንሣኤውን እውነት ለዓለም ሁሉ ይገልጽ ዘንድ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል
በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን መካከል ተለይቶ በክብር ተነሣ። መቃብሩም ባዶ ሆነ። እንኳን ደስ
አላችሁ። እንኳን ደስ አለን።

ምንም እንኳን የመቃብሩ ጠባቂዎች ጥቂት መደለያ (እጅ መንሻ ተቀብለው ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀው
ወሰዱት ብለው እንዲያወሩ ተደርገው ወሬው ከተማውን ሁሉ ቢያጥለቀልቀውም በኩረ ትንሣኤ ከርስቶስ
ግን ከተነሣ በኋላ ትንሣኤው እሙን መሆኑን ለነ ማርያም መግደላዊት በመታየት፣ ለሐዋርያት በተለያየ
ጊዜ ለኬፋም ለዐሥራ ሁለቱም፣ ከዐምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች ባንድ ጊዜ በመታየት የአይሁድን
ሴራ መና እንዳስቀረ ሐዋርያው ጳውሎስ በስፋት ጽፎልናል። (ቆሮ 15፡58)። በተዘጋ ቤት ገብቶ ሰላም
ለናንተ ይሁን ብሎ ሰላምን ሰብኮላቸዋል። ምትሀት አለመሆኑን ለመግለጽ የተቸነከረበትን እጁን እግሩን፣
በጦር የተወጋውን ጎኑን አሣይቷቸዋል። በመቃብሩ ቦታ የተገኙ መላእከትም ሕያውን ከሙታን መካከል
ስለ ምን ትፈልጋላችሁ ተነሥቷል እንጂ በዚህ የለም (ሉቃ 24፡5) ሲሉ የትንሣኤውን ኃይል ገልጸዋል።
የትንሣኤው ችቦ በሐዋርያት እየተቀጣጠለ ለዓለም ሁሉ በማብራቱ የአይሁድ ሀሰት ተጋለጠ። የክርስቶስ
ትንሣኤ ለኛ ትንሣኤም በኩር በመሆኑ እስከምጻት ሲነገርና ሲታመን ይኖራል። እኛም ዛሬ የሐዋርያትን
ጆሮ ጆሮ አድርገን ዐይኖቻቸውንም ዐይኖቻችን አድርገን ትንሣኤውን በደስታ እያከበርን እንገኛለን።

በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ።

ውድ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ

ይህ በዓል መንፈሳዊ በዓል እንደመሆኑ ከአልባሌ ነግር ርቀን አብዝቶ ከመብላትና ከመጠጣት ተቆጥበን
ምንም የሌላችውን፣ አባት እናት የሞቱባቸውን፣ በተለያዩ ደዌ ተይዘው በየሆስፒታሉ፣ በየጸበል ቦታውና
በየቤታቸው ሆነው በዓሉን እንደኛ ማክበር የተሳናቸውን፣ በሕግ ጥላ ሥር ሆነው በማረሚያ ቤት ያሉትን
በመጎብኘትና ካለን ላይ ከፍለን በማብላት ልናከብረው ይገባል፡፡

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን

በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን

አሰሮ ለሰይጣን

አግዐዞ ለአዳም

ሰላም

እምይእዜሰ

ኮነ

ፍስሐ ወሰላም።

አባ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *